በዚህ ሳምንት የተመለከትናቸውን ዐበይት ተጫዋች ነክ ጉዳዮች እንዲህ አሰናድተናል።
👉 እናቱን ያሰበው መስዑድ መሐመድ
በ15ኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰበታ ከተማ ሀዋሳን 2-1 ሲረታ ለሰበታ ከተማ ሁለተኛዋን ግብ መስዑድ መሐመድ ማስቆጠሩ ይታወሳል።
የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ግቡን ያስቆጠረው የሰበታ ከተማው አምበል ግቧን ካስቆጠረ በኋላ የቅልጥም መከላከያ (መጋጫውን) አውጥቶ አስቀድሞ በእስክሪብቶ የፃፈውን እና ከአንድ ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን እናቱን ያሰበበትን ፅሁፍ በማሳየት ደስታውን ልብ በሚነካ መልኩ መግለፅ ችሏል።
👉 ከጎል የታረቀው ሙጂብ ቃሲም
በ9ኛ የጨዋታ ሳምንት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ፋሲል ከነማ ወልቂጤ ከተማን 1-0 ሲረታ ሙጂብ ቃሲም ነበር በፍፁም ቅጣት ምት በ84ኛው ደቂቃ የቡድኑን የማሸነፍያ ግብ ያስቆጠረው። በፈታኙ ጨዋታ ቡድኑን ለድል ያበቃችው ግብ ሙጂብ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራት 12ኛ ግብ ሆና ተመዝግባም ነበር።
ታድያ በከፍተኛ ግብ አግቢነቱ ፉክክርን ይመራ የነበረው አጥቂው 12 ግቦች ከደረሰ በኃላ በነበሩት ተከታታይ አራት የጨዋታ ሳምንታት እንደቀሙት ሳምንታት ምርታማ አልነበሩም። በዚህም በሁለተኝነት ይከተለው በነበረው አቡበከር ናስር ተበልጦ በሁለተኛ ደረጃ ለመቀመጥም ተገዷል።
በዚህ ሒደት ውስጥ እሱ ግብ አያስቆጥር እንጂ ቡድኑ የሊጉ መሪነቱን አጠናክሮ ቢቀጥልም የፊት አጥቂያቸውን ወደ ግብ አግቢነት መመለስ በዐፄዎቹ ቤተሶቦች ዘንድ በጉጉት ይጠበቅ ነበር። ሙጂብም 13ኛውን ግብ እጅግ ወሳኝ በነበረው እና ተከታያቸውን በረቱበት ጨዋታ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ በማስቆጠር ለቡድኑ አለኝታ መሆኑን ዳግም አስመስክሯል።
👉 ፍፁም ገብረማርያም ወደ ቀደመው አስፈሪነቱ እየተመለሰ ይመስላል
በኢትዮጵያ እግርኳስ በአንድ ወቅት ከፍ ያለ ቦታ ይሰጣቸው ከነበሩ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው እና አስገራሚ እምርታ አሳይቶ የነበረው የእግርኳስ ህይወቱን የከፍታ ጉዞ ማስቀጠል ተስኖት የቆየው ፍፁም ገ/ማርያም በመጠኑም ቢሆን ያን የቀደመ የአጥቂ ደመነፍሱን መልሶ እያገኘው ይመስላል።
በወለጋ ዩኒቨርስቲ የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ ከመላው ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውድድር አንስቶ በሙገር ሲሚንቶ ይበልጥ ጎልብቶ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው አጥቂው በፈረሰኞቹ ቤት ወጣ ገባ ጊዜያትን ካሳለፈ ወዲህ ያልተረጋጋ ቆይታን በተለያዩ ክለቦች አድርጎ አሁን ላይ አንጋፋዎችን ከወጣቶች የቀላቀለው የሰበታ ከተማን ፊት መስመር እየመራ ይገኛል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከግብ አግቢነቱ ይልቅ ፊት መስመር ላይ በሚያደርገው ጥረት የሚታወሰው ተጫዋቹ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ግን የተሻለ እየተነቃቃ የሚገኝበት ይመስላል።
ሰባት ግቦችን እስካሁን ማስቆጠር የቻለው አጥቂው እጅግ ወሳኝ በሆኑ የጨዋታ ቅፅበቶች ሳጥን ውስጥ የሚገኝበት መንገድ እጅግ አስደማሚ እየሆነ መጥቷል። በተጨማሪም እያስቆጠራቸው የሚገኙ ግቦች የመጨረሻ አጥቂ ባህሪ የተላበሱ ተጨዋቾች የሚያስቆጥሯቸው ዓይነት መሆናቸው ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም ወደምናወቀው ማንነቱ የመመለስ ፍንጮችን እያሳየን ይገኛል ለማለት ያስደፍራል። በዚህ መሻሻሉ ቀጥሎ የቀደመውን ያንን አስደናቂ አጥቂ ዳግም እንመለከተው ይሆን ?
👉 ከየካቲት እስከ የካቲት – አህመድ ሁሴን
ከጎል ጋር ፀብ ውስጥ ገብቶ የከረመው የወልቂጤው የፊት አጥቂ ከአንድ ዓመት በኃላ ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋርን ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸንፍ ያስቻለች ግብ በማስቆጠር እርቅ አውርደዋል።
ተደጋጋሚ የመሰለፍ ዕድሎችን ቢያገኝም ፤ አስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የግብ አጋጣሚዎችን ቢፈጥርም ፣ ግብ ለማስቆጠር በተመቹ ቦታዎች እና ቅፅበቶች መገኘት ቢችልም የመጨረሻ ውሳኔዎቹ ግን “እንዴት ሊስተው ቻለ ?” ስንል እንድንጠይቅ የሚያስገደዱ ነበሩ።
ፈጣኑ አጥቂ በተሰረዘው የውድድር ዘመን በወርሃ የካቲት ወልዋሎ ላይ ግብ ካስቆጠረ ወዲህ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለ15 የጨዋታ ሳምንታት ያለ ግብ ሊቆይ ችሏል። እንደ አጥቂ እጅግ ፈታኝ ጊዜን ላሳለፈው ተጫዋች ይህች ግብ የራስ መተማመኑን መልሶ እንዲያገኝ ልታግዘው ትችላለች ተብሎ ይጠበቃል።
👉 ጋቶች ፓኖም ከጎል ጋር ተመልሷል
በ2009 መጨረሻ ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ ወደ ሩሲያው በአንድ ወቅት ገናና ወደ ነበረው ኦንዢ ማካቻካላ ከተዘዋወረበት ጊዜ እንስቶ በግብፆቹ ሆራስ አልሁዳድ እና ኤል ጎና እንዲሁም በሳውዲ አረቢያው አል አንዋር የተጫወተው ግዙፉ አማካይ በመሀል በ2010 የውድድር ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በመቐለ 70 እንደርታ ቆይታ ማድረጉ ይታወሳል።
ተጫዋቹ ከመጨረሻው ክለቡ በስምምነት ከተለያየ በኋላ ከቀናት በፊት ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ወላይታ ድቻን ተቀላቅሏል። ለአራት ወራት ያህል ከፉክክር ጨዋታ ርቆ የነበረው ጋቶች ባሳለፍነው ሳምንት ከሥራ እና መኖርያ ፍቃድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መጠናቀቀቸውን ተከትሎ ቡድኑ አዳማን በገጠመበት ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለቡድኑ አድርጓል።
በመጀመሪያ 11 ውስጥ በመግባት ጨዋታውን የከወነው አማካዩ ጥሩ እንቅስቃሴን ከማድረግ ባለፈ ከፍተኛ መሻሻል ላይ የሚገኘውን ቡድኑን የከፍታ ጉዞ ያስቀጠለች ብቸኛ የማሸነፊያ ግብ በማስቆጠር አስደሳች አጀማመር አድርጓል።
👉አቡበከር ኑሪ – የዳንኤል አጃይ አልጋ ወራሽ?
በ2010 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባደጉበት ዓመት ጅማ አባ ጅፋሮች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ዋንጫ ሲያነሱ ጋናዊው ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጃዬ እጅግ ድንቅ ጊዜን አሳልፏል። በቀጣዩ የውድድር ዘመን በአፍሪካ መድረኮች እና በሊጉ ደካማ እንቅስቃሴ ባደረገው ጅማ አባ ጅፋር ውስጥ ይህ ጋናዊ በግሉ ለቡድኑ የተቻለውን ማድረጉ አይዘነጋም። ከአጄዬ በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ ጅማ ሁነኛ የግብ ዘብ ያገኘ ይመስላል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተካፋይ ከሆነው ወሎ ኮምቦልቻ ጅማ አባ ጅፋርን የተቀላቀለው አቡበከር ኑሪ ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ በሊጉ ባገኘው የመሰለፍ ዕድል ቡድኑ እንደተሰነዘረበት ተደጋጋሚ ጥቃት በጠባብ ውጤት ተሸንፎ እንዲወጣ ማድረግ ችሏል። ምንም እንኳን ሁለት ግቦችን ቢያስተናግድም ከአምስት በላይ ግብ መሆኑ የሚችሉ አደገኛ ሙከራዎችን ማዳን ችሏል።
ይህን ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው አልነበረም። ከጥቂት የጨዋታ ሳምንታት በፊት ቡድኑ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የመጀመሪያ ጨዋታ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ሲያሳካ እንዲሁ በግሉ በርካታ ኳሶችን አድኖ ለቡድኑ ውጤት ማማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
እርግጥ ሁለቱን ተጫዋቾች ማነፃፀር ተገቢ ባይሆንም በአስደናቂ አጀማመር ላይ የሚገኘው ይህ ወጣት ግብ ጠባቂ በዳንኤል አጄይ ደረጃ በተቀመጠው የጅማ የግብ ጠባቂዎች ከፍታ መገኘት ይችል ይሆን ? የሚለው የሚጠበቅ ይሆናል።
👉 አስደንጋጩ የታሪክ ጌትነት አደጋ
ወላይታ ድቻ ከአዳማ ከተማ ባደረጉት የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ በ64ኛው ደቂቃ እጅግ አስደንጋጭ የነበረ ጉዳትን አስተናግዷል።
የአዳማ ከተማዎቹ ታሪክ ጌትነት እና አሚን ነስሩ ኳስን ለማግኘት በተጋጩበት ቅፅበት ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ምላሱ ተንሸራቶ የመተንፈሻ አካሉን በመዝጋቱ አስጊ የሚባል አደጋ አጋጥሞት ነበር።
በዚህም ሒደት የቡድን አጋሮቹ ደሳለኝ ደባሽ እና በላይ ዓባይነህ ተጫዋቹ ምላሱን ወደነበረበት በመመለስ ታድገውታል። ግብጠባቂው ራሱን መሳቱን ተከትሎ በሁኔታው ሜዳው ላይ ካሉ ተጨዋቾች ውጪ ተጠባባቂዎች እና ሌሎች የጨዋታው አካል የሆኑ ግለሰቦች ሜዳ ውስጥ በከፍተኛ ድንጋጤ ተውጥተውም ታይተዋል።
ዘጠኝ ደቂቃዎችን ከፈጀው የሜዳ ላይ የመጀመሪያ ዕርዳታ በኋላም ታሪክ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ሆስፒታል ለተጨማሪ እርዳታ አምርቷል። አሁን ላይም ተጫዋቹ በተሻለ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል።
👉 ሣላምላክ ተገኘ – ገባ… አገባ
ባህርዳር ከተማን ከሀዲያ ሆሳዕና ባገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ መርሃግብር ሁለቱ ቡድኖች ለ63 ያህል ደቂቃዎች 0-0 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን እየገፉ ይገኙ ነበር።
ቡድኖቹ ከጨዋታው አንዳች አውንታዊ ውጤትን ይዘው ለመውጣት ጥረት በሚያደርጉበት በዚያ ወቅት የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በመስመር በኩል ያለው የማጥቃት ሂደት ለማሻሻል የመስመር አማካዩ ግርማ ዲሳሳን በሣላምላክ ተገኘ ለመቀየር ይወስናሉ። ቅያሬው በ62ኛው ደቂቃ ተደርጎ ግርማን የተካው ሣላምላክ ተገኝ ከ100 ሰከንድ ያነሰ የሜዳ ላይ ቆይታ በኋላ ግን ከሳምሶን ጥላሁን የደረሰውን ኳስ በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። የእሱ ግብም ቡድኑ በሰንጠረዡ ላይ መሻሻልን ያመጣበት እና ሁለተኛ ተከታታይ ድል የተመዘገባባት ብቸኛ ግብ ሆና አልፋለች።
© ሶከር ኢትዮጵያ