ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የቁምነገር ካሣ ብቸኛ ጎል ድሬዳዋን ባለድል አድርጓል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አስራ አምስተኛ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ መካከል ተደርጎ ድሬዳዋ 1 ለ 0 አሸንፏል።

በመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝነት ያለው ፉክክር ማየት ብንችልም በሙከራ ረገድ ግን ድሬዳዋዎች ተሽለው ታይተዋል፡፡ እታለም አመኑ ከርቀት በሞከረችው ሙከራ ቀዳሚውን የግብ አጋጣሚ ለመፍጠር የጣሩት ድሬዎች በመስመር አጨዋወት ተደጋጋሚ ጥቃትን ሲያደርሱ ታይቷል፡፡

ታደለች አብርሃም በቀኝ በኩል በጥሩ የመስመር አጨዋወት የተገኘችን አጋጣሚ በግራ እግሯ በቀጥታ መታ ቤተልሄም ዮሀንስ የያዘችባት እና 28ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ትንቢት ሳሙኤል አማካኝነት ግልፅ ዕድልን አግኝታ ቤተልሄም የያዘችባት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

በእንቅስቃሴ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ቢኖራቸውም ወደ ድሬዳዋ ግብ ክልል ደርሶ ሙከራ ለማድረግ ያልታደሉት አዲስ አበባ ከተማዎች በተቃራኒው 43ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል የተሻማን ኳስ ዮርዳኖስ ፍሰሀ ኳስን ለማውጣት ባደረገችው ውሳኔ ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ በራሷ ላይ ለጥቂት ብረት መለሰባት እንጂ አዲስ አበባ ከተማዎች በራሳቸው ላይ ባስቆጠሩ ነበር፡፡

ከመልበሻ ክፍል ቡድኖቹ ሲመለሱ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የሙከራ ብልጫ የታየባቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ነበሩ። ድሬዎች ይታይባቸው የነበረውን ደካማ የአጨራረስ ክፍተት ለመቀልበስ ቁምነገር ካሣን እና በመጀመሪያው አጋማሽ 28ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ከገባችው ትንቢት ሳሙኤል ጋር በማቀናጀት የነበረባቸውን ክፍተት ለመድፈን ሙከራን አድርገዋል፡፡ አጋማሹ ከተጀመረ አራት ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ታደለች አብርሀም ባደረገችው ሙከራ አዲስ አበባ ላይ ጫናን ማሳደር ቀጥዋል። ፀሀይነሽ በቀለ ወደ ጎል ለማሻማት ባደረገችው ጥረት የግቡ የላይኛው ብረትን ነክታ የወጣችባት ለድሬዳዋ የሙከራ ብልጫ ሌላኛዋ ማሳያ ነች፡፡ በአንፃሩ ቤተልሄም ሰማን በጥሩ ቅብብል የመጣን ኳስ አግኝታ በቀጥታ መታ የሳተችው ብቸኛ የአዲስ አበባ የሁለተኛው አጋማሽ የጎላ ሙከራ ነበር፡፡

ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት ፍሬ አፍርቶ 85ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋነሽ ወራና ወደ ግብ ክልል እየገፋች ገብታ ነፃ አቋቋም ለነበረችው ቁምነገር ካሣ ሰጥታት አጥቂዋ ወደ ጎልነት ለውጣው ክለቧን መሪ አድርጋለች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች አዲስ አበባ ከተማዎች አቻ ለመሆን ጥርት ቢያደርጉም ብዙም ስኬታማ እንዲሆኑ አላስቻላቸውም፡፡

መደበኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው አስደንጋጭ አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ የድሬዳዋ ከተማዋ የመሐል ተከላካይ ብርቄ አማረ ከአዲስ አበባ ከተማዋ ተጫዋች መስታወት ጋር ኳስ ለመንጠቅ ባደረጉት ፍትጊያ ተከላካይዋ የማዕዘን መምቻው ጋር ባለው የሜዳው ክፍል ላይ በሀይል በመገፍተሯ ለመውደቅ ተገድዳለች። በዚህም በጭንቅላቷ አካባቢ ጉዳትን አስተናግዳለች። ተጫዋቿ በወደቀችበት ሰዓት ከህክምና ባለሙያዎች በተሻለ የውድድር ኮሚቴው አባል ዶክተር እንደገና አለምአዋሶ እና ኮሚሽነር ሳራ ሰዒድ ለተጫዋቿ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታን ለመስጠት ያደረጉት ጥረት የሚያስመሰግን ሲሆን ተጫዋቿም ለተሻለ ህክምና በቶሎ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል አምርታለች፡፡

ጨዋታው ቀጥሎ ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በድሬዳዋ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ጉዳት የገጠማት ተጫዋቿ በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ አረጋግጣለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ