ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የጨዋታ ሳምንቱን ትኩረት የምጠቃልለው በአራተኛው ክፍል መሰናዶ ነው።

👉 የተላላጠው የተጫዋቾች ስም ፅሁፍ

በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተመለከትነው ከሚገኘው አዲስ ልምምድ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ሁሉም ክለቦች በሚጠቀሟቸው መለያዎች ጀርባ የተጫዋቾች ስያሜ ታትሞ የመመልከታችን ጉዳይ ነው።

የሚፃፍበት መንገድ (ፎንት) ፣ የቀለማት ምርጫ እና የፅሁፎች መጠን (ፎንት ሳይዝ) ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ መሻሻል ይገባል በሚል ሀሳቦችን ስናነሳ ቆይተናል። አሁን ደግሞ በዚህኛው ሳምንት የትኩረት ነጥባችን ስለተላላጠው ብሎም ስለጠፋው የተጫዋቾች ስም ሀሳቦችን ለመሰንዘር ወደናል።

በሊጉ ከሚገኙ ክለቦች በታሪክም ሆነ በስኬት በቅዱስ ጊዮርጊስ ደረጃ የሚስተካከል ቡድን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። ይህ ክለብ እንደ ታሪክ ከፍታው በብዙ ነገሮች ከብዙዎች ተሽሎ መገኘት ይጠበቅበታል። በመጀመሪያው ዙር በተጫዋቾች መለያ ላይ የተጫዋቾች ስያሜን ሊያሰፈረው ቡድኑ ከጥቂት የጨዋታ ሳምንታት በፊት ግን በተጫዋቹ መለያ ላይ ስማቸው እንዲታተም ማድረጉ አይዘነጋም። ነገር ግን ህትመቱ ከቀናት የዘለቀ ቆይታ ያለው አይመስልም።

በደካማ የጥራት ደረጃ የታተመው ይህ ፅሁፍ ከወዲሁ ተላላልጦ የአንዳዶቹ ከነጭራሱ ተልጦ ባዶ ሆኖ እየተመለከትን እንገኛለን። ይህ ሂደት በተለይ በቴሌቪዥን መስኮት በሚተላለፈው በዚህ ውድድር የክለቡ ምስል ላይ ዓይነተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነውና የክለቡ ሰዎች ጉዳዩን በደንብ ሊያጤኑት ይገባል።

👉በውድድር አጋማሽ አዲስ መለያ አስፈላጊ ነውን ?

መለያዎች የሚወክሉትን ክለብ ከመግለፃቸው ባለፈ በራሳቸው ታሪክን የመናገር አቅም እንዳላቸው ይታመናል ። በተለይ በሌሎች ሀገራት ቡድኖች ለአንድ የውድድር ዘመን ሦስት መለያዎችን (የመጀመሪያ ፣ ሁለተኛ እና አማራጭ) ይጠቀሙና በቀጣዩ የውድድር ዓመት እነዚሁን ሦስት መለያዎች ላይ የንድፍ (design) ለውጥ አድርገው መቅረባቸው የተለመደ ነው።

በዚህ ሒደት የቡድኑ ደጋፊዎች የክለቡ ስኬትም ሆነ ውድቀት እንዲያው በጥቅሉ የክለቡ የታሪክ ዑደትን በውድድር ዘመኑ ከሚጠቀማቸው መለያዎች ጋር ሲያስተሳሩት ይስተዋላል። ይህ ልምድ በሀገራችን በተወሰኑ መልኩ የሚስተዋል ነው።

ታድያ መለያ የክለቦች የታሪክ መገላጫ ስለመሆኑ ግን በሀገራችን ያለው ግንዛቤ እጅግ አናሳ ነው። ክለቦች በውድድር ዘመን የመለያዎች ወጥነት በአንዳንድ ሊጎች በደንብ ላይ ሁሉ መካተት ደረጃ በተደረሰበት በዚህ ወቅት በሀገራችን ባለው ደካማ የእግርኳስ እና የቢዝነስ አረዳድ ቡድኖች በውድድር ዘመን መለያቸውን ባሻቸው መጠን በፈለጉበት ወቅት የመቀየር ነፃነት እየተጠቀሙ እንዳሻቸው ሲቀያይሩ ይስተዋላል።

ለማሳያነትም አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ለዚህ ሂደት ዓይነተኛ ምሳሌ ሆነው መቅረብ የሚችሉ ናቸው። በእኛ ሀገር ባለው ልማድ ክለቦች በጀት በተለቀቀላቸው ወቅት ወደ ገበያ ወጥተው መለያ ይቀይራሉ እንጂ ወጥ የሆነ ይህን ስርዓት የሚያሲዝ የህግ ማዕቀፍም ስለመኖሩ ያጠራጥራል።

ለዚህ ሁሉ መነሻ የሆነን በአዳማ ከተማ ቤት እያስተዋልን የምንገኘው ነው። ሁለት መለያዎችን በመጀመሪያው የውድድር አጋማሽ የተጠቀሙት አዳማ ከተማዎች በሁለተኛ ዙር ደግሞ ከመጀመሪያዎቹ በተወሰነ መልኩ በቀለምም ለወጥ ያሉ ሁለት መለያዎችን ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሲጠቀሙ አስተውለናል።

አዳዲስ መለያዎች በውድድር አጋማሹ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ይልቅ በአዲሱ የውድድር ዘመን በአዲስ መንፈስ በአዲስ ገፅታ መቅረብ በሌላው ሀገር ቢለመድም ከዘመናዊ እግርኳስ ለመታረቅ አሻፈረኝ ያለው እግርኳሳችን ግን በጀት ከተገኘ በአንድ የውድድር ዘመን እንደፈቀደህ መለያ በመቀያየር ጉዞው እንደቀጠለ ነው።

👉 የውበቱ አባተ በጨዋታ ተንታኝነት ብቅ ማለት

በኢትዮጵያ እግርኳስ በአሁኑ ወቅት በማሰልጠን ላይ ከሚገኙ እና እግርኳስን በላቀ ደረጃ ከሚረዱ እና በተሻለ መንገድ ሀሳባቸውን መግለፅን ከተካኑ ጥቂት አሰልጣኞች አንዱ የሆኑት አሰልጣኝ ውበቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ከሚዲያው በተወሰነ መልኩ ጠፋ ብለው ነበር።

እንደአሁኑ በሊጋችን በድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው ሜዳ ላይ በነበሩ ሁነቶች ላይ ያተኮረን አስተያየት ብቻ የሚሰጡ አሰልጣኞች ብቅ ብቅ ከማለታቸው በፊት በነበሩት ዓመታት በድህረ ጨዋታ አስተያየቶቻቸው በሚያነሷቸው እግርኳሳዊ ሀሳቦች በብዙዎች ይወደዱ የነበሩት የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በ15ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን በነበሩት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ፣ በዕረፍት ሰዓት እንዲሁም ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሱፐር ስፖርት ቀርበው በጨዋታዎቹ ዙርያ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አሰልጣኝ ውበቱ እና ረዳቶቻቸው እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በዚህ የጨዋታ ሳምንት በስታዲየም ተገኝተው የጨዋታዎችን ተከታትለዋል።

👉 ለዕይታ ፈታኝ የነበረው ጨዋታ

በ15ኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ በከሰዓቱ መርሐ-ግብር ጅማ አባ ጅፋርን ከወልቂጤ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ባልተለመደ መልኩ ሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ ቀለም ያላቸውን መለያ የተጠቀሙበት ነበር።

ጅማ አባጅፋር ሙሉ ቀይ መለያ ከቀይ ካልሲ ጋር ሲጠቀም በአንፃሩ ወልቂጤዎች የመጀመሪያ ምርጫቸው የሆነውን ብርቱካናማ መለያን በሰማያዊ ካልሲ ሲጠቀሙ ተመልክተናል።

በጨዋታው ዕለት የሁለቱ ቡድኖች የመለያ ቀለም እጅግ ከመቀራረቡ የተነሳ ለዕይታ እጅግ አስቸጋሪ የነበረበት ጨዋታ ነበር። በቅድመ ጨዋታ ውይይት ወቅት ጨዋታውን የመሩት ዳኞች እና የጨዋታ ታዛቢ ይህን እንዴት ሊፈቅዱ ቻሉ የሚለው ነገር በትልቁ ጥያቄ የሚያስነሳ ነበር።

ሁለቱ ቡድኖች አማራጭ መለያዎችን ማቅረብ ስላልቻሉ ወይስ በቸልተኝነት የተሰራ ስህተት ነው የሚለው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው።

👉 የጨዋታ ዕለት ድጋፍን አዲስ ገፅታ ያለባሱት ዕንስት ደጋፊዎች

ወልቂጤ ከተማ ጅማ አባጅፋርን ከመመራት ተነስቶ ባሸነፈበት ጨዋታ በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ለየት ያለ የደጋፊዎች ስብጥር እና አደጋገፍ ተመልክተናል።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን በየትኛውም ጨዋታ ከተመለከትናቸው ጨዋታዎች በተለየ በቁጥር በርከት ያሉ ሴት ደጋፊዎችን በወልቂጤ ከተማ መለያ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ተመልክተናል።

በዚህ ቁጥር ከወንዶች ልቀው ሴቶች ቡድናቸውን ሲያበረታቱ መመልከት በራሱ የሚበረታታ ሲሆን በዕለቱ ያሳዩት ድጋፍ እና ስሜታቸውን ለመግለፅ ያወጧቸው የነበሩት ድምፆች በስታድየሞቻችን ከተለመደው ወጣ ያለ መሆኑ በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ