ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የሀዋሳ እና አቃቂ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአስራ አምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ከአቃቂ ቃሊቲ ጋር 1ለ1 ተለያይቶ ለዋንጫ የነበረውን ጉዞ አደብዝዟል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኳስን በመቆጣጠር እና የመሐል ሜዳውን ክፍል በመጠቀሙ አቃቂ ቃሊቲዎች እጅጉን የተሻሉ ሆነው ታይተዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች ካለፉት ጨዋታዎቻው እና ካሉበት ደረጃ አንፃር በተሻለ ብልጫ ይኖራቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም በተቃራኒ በተጋጣሚያቸው ሊበለጡ ግድ ሆኗል፡፡ ገና ጨዋታው በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃም መሳይ ተመስገን ሀዋሳን መሪ ልታደርግ የምትችል ያለቀለትን ዕድል አግኝታ ስታዋለች፡፡

መሀል ሜዳ ላይ አቃቂዎች ብልጫን እንዲይዙ በተሻለ የመጫወት ፍላጎት ደምቃ የዋለችው ኪፊያ አብዱራህማን ሀዋሳዎች ለማጥቃት ወደ ፊት በሄዱበት ሰዓት የኃላ መስመራቸው በመጋለጡ 11ኛው ደቂቃ ከቤዛዊት ንጉሴ ያገኘችውን የመልሶ ማጥቃት ኳስ በአግባቡ ወደ ጎልነት ለውጣው ክለቧን መሪ አድርጋለች፡፡

በተረጋጋ እና በተቀናጀ የአጨዋወት መንገድ ከመጫወት ያልቦዘኑት አቃቂዎች ተጨማሪ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል፡፡ 21ኛው ደቂቃ ላይ አምበሏ አስናቀች ትቤሶ ከቅጣት ምት በቀጥታ መታ ግብ ጠባቂዋ ገነት ኤርሚያስ ስትተፋ ኪፊያ ሁለተኛ ግብ አስቆጠረች ሲባል ስታዋለ፡፡ ከዚህች ሙከራም በኃላ በቤዛዊት ንጉሴ አማካኝነት መሞከር ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ለማከል ግን አልቻሉም፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አራት ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ እያለ ረጅሙን ደቂቃ ፈዘው የዋሉት ሀዋሳ ከተማዎች ከመሀል ሜዳው ወደ ግራ የአቃቂ ግብ ክልል ባደላ ቦታ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ከግምት 40 ሜትር ርቀት አክርራ በመምታት መሳይ ተመስገን በግሩም ሁኔታ አስቆጥራ ሀዋሳን 1ለ1 በማድረግ ለእረፍት ወጥተዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር በኳስ ቁጥጥሩ አቃቂዎች ተሽለው ቀርበዋል፡፡ በእንቅስቃሴ ይብለጡ እንጂ በሙከራ ረገድ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሀዋሳዎች ተሽለዋል፡፡ የጨዋታው ፍሰት ጥሩ የነበረ ቢሆንም የረዳት ዳኞች አጨቃጫቂ ውሳኔዎች እና ከመሐል ዳኛዋ ጋር ያለመናበብ ሁኔታ ጨዋታውን አደብዝዘውት ታይቷል፡፡

የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ረጃጅም ኳስን ሲጠቀሙ የነበሩት ሀዋሳዎች በምስር ኢብራሂም እና ረድኤት አስረሳኸኝ አማካኝነት ሙከራን ማድረግ ችለዋል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ሳራ ኬዲ ያለቀለትን ኳስ አግኝታ ሀዋሳን አሸናፊ ልታደርግ የነበረች አጋጣሚ ብትሆንም ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ ይዛባት ጨዋታው 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተደምድሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ