​ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

16ኛው ሳምንት የሚጀምርበትን ጨዋታ የዳሰሳችን ቀዳሚ ትኩረት አድርገነዋል።

ያሳለፍነውን የጨዋታ ሳምንት በአሸናፊነት ያሳለፉት ወልቂጤ እና ድቻ በጥሩ መንፈስ ላይ ሆነው የሚገናኙበት የነገው ጨዋታ ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እንደሚደረግበት ይጠበቃል። በጨዋታ ረገድ መጥፎ ያልነበረው ወልቂጤ ከውጤት ጋር ተራርቆ ዳግም ወደ ሦስት ነጥብ በተመለሰበት የጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ የዘወትር ታታሪነቱ አብሮት ነበር። ወላይታ ድቻም ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አዳማ ላይ አስመዝግቦ የዘንድሮ አካሄዱን በማሳመሩ ገፍቶበታል። አሁን ላይም ሁለቱ ቡድኖች በሰንጠረዡ ወገብ ተከታታይ ደረጃ ላይ ሆነው ወደ ላይኛው ፉክክር ለመቃረብ ከነገው ጨዋታ የሚገኘውን ውጤት ይጠባበቃሉ።

ወልቂጤ ከተማ ጅማን ሲረታ ፊት መስመር ላይ ያለበትን የአጨራረስ ችግር ለማቃለል ተስፋ የሚሰጥ ጨዋታንም ነበር ያሳለፈው። የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ትዕግስት ፍሬ ባፈራበት በዛ ጨዋታ አህመድ ሁሴን ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ግብ ማስቆጠሩ ከመመለሱ ባለፈ አሜ መሀመድም እንደ ከዚህ ቀደሙ የተሻለ የመጨረስ ብቃት ያለው መሆኑን የሚያሳይ ግብ በስሙ አስመዝግቧል። ያም ቢሆን ቡድኑ ነገ ግብ ካስተናገደ አራት ጨዋታዎችን ካሳለፈው ድቻ ጋር እንደመጫወቱ እና አሜ መሀመድም በጉዳት ባለመኖሩ በጅማ ተስፋ የሰጠው የፊት መስመሩ ስልነት ዳግም የሚፈትን ይሆናል። 

ከኋላ ያለው የወልቂጤ ከተማ ችግር ግን አሁንም ለስጋት የሚያጋልጥ ነው። በጅማው ጨዋታም እንዲሁ በትኩረት ማነስ ግብ ያስተናገደው የወልቂጤ የተከላካይ ክፍል ከፈጣን አጥቂዎች ጋር ሲገኝ መቸገሩን የቡናውም ጨዋታ አሳይቶናል። ይህ ደካማ ጎን ደግሞ በመልሶ ማጥቃት አስፈሪ ከሆነው የነገ ተጋጣሚው ጋር ሲገናኝ ዳግም ለስህተት ከተዳረገ እና ግብ ከተቆጠረበት በቀላሉ የማይሰበረውን ድቻን ከኋላ ተነስቶ ለማሸነፍ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል። ከዚህ በተለየ አማካይ ክፍል ላይ ከፍተኛ ፍልሚያ እንደሚደረግ በሚጠበቅበት ጨዋታ ቡድኑ በአብዱልከሪም ወርቁ እና በኃይሉ ተሻገር የፈጠረው ጥምረት በጅማው ጨዋታ መጠን ከሰመረ በመስመሮች መካከል ክፈተት በማይተወው የድቻ አደረጃጀት ውስጥ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አቅም እንደሚኖረው ይገመታል።

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ከቀጠረ አንስቶ ውጤት ያዘነበለለት ወላይታ ድቻ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ መጣሉ ወቅታዊ አቋሙን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በዚህ ላይ ደግሞ በጨዋታዎቹ ሁለት ጊዜ ብቻ መረቡ መደፈሩ ይበልጥ የቡድኑን የጥንካሬ ምንጭ የሚያሳየን ነው። የድቻ የኋላ አራት ተጫዋቾች ጥምረት ሳይለዋወጥ መዝለቁ እንደ ቡድን ለተከላካይ ክፍሉ በቂ ሽፋን ከመስጠቱ ጋር ተዳምሮ የመከላከል ሪከርዱን አስገራሚ አድርጎታል። የነገው ጨዋታ ደግሞ በቅርብ ጨዋታዎች በማጥቃቱ ረገድ ተዳክሞ በመጨረሻ ጨዋታው ከተነቃቃው ወልቂጤ ጋር መሆኑ እዚህ ቦታ ላይ የሚኖረውን የጨዋታውን ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል።

ወላይታ ድቻ በደካማ ጎን የሚነሳው ችግሩ የግብ ዕድሎችን ከክፍት ጨዋታዎች በማግኘት በኩል ያለበት እክል ነው። ለኳስ ቁጥጥር የተሻለ ፍላጎት ባሳየበት የአዳማው ጨዋታም ቡድኑ ዕድሎችን መፍጠር ከብዶት ታይቷል። ይልቁኑም በመልሶ ማጥቃት ረገድ የተሻለ አስፈሪነት የሚታይበት ድቻ ከተጋጣሚዎች አቀራረብ አንፃር ራሱን ስለሚቀያይርም የአዳማውን የጨዋታ ዕቅድ ነገ ይተገብረዋል ተብሎ አይገመትም። ከወልቂጤ የኋላ መስመር ክፍተት አንፃርም የቢኒያም ፍቅሬ እና ፀጋዬ ብርሀኑ ፍጥረት ለቡድኑ የተሻለ ዕድልን ሊፈጥርለት ይችላል። በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች በተጠባባቂነት የተመለከትነው ስንታየሁ መንግሥቱም የጨዋታ ደቂቃዎችን ካገኘ በፈጣን ሽግግር ግብ ላይ ለመድረስ ጥሩ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። አሁንም ግን የቆሙ ኳሶችን የሚጠቀሙበት መንገድ የጦና ንቦቹ  ጠንካራ ጎን መሆኑን ሳያስታውሱ ማለፍ የማይታሰብ ነው።

በነገው ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ከፍሬው ሰለሞን እና አሳሪ አልመሀዲ በተጨማሪ አሜ መሀመድንም በጉዳት ሲያጣ በወላይታ ድቻ በኩል ከአስናቀ ሞገስ ጉዳት ውጪ ቀሪው ስብስብ ሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል። ከዚህ ውጪ የወልቂጤው ጀማል ጣሰው እና የወላይታ ድቻው በረከት ወልዴ ከቅጣት መመለስ በሁለቱም በኩል ትልቁ የቡድን ዜና ነው። ጀማል እርሱ በሌለበት አደረጃጀቱ የተፋለሰውን የኋላ ክፍል እንደሚያስተካክል ተስፋ የሚጣልበት ሲሆን የድቻው ቁልፍ አማካይ በረከት ቅጣት ላይ በሰነበተበት ወቅት ጥሩ ጊዜ ካሳለፉት የቡድኑ አማካዮች እንዲሁም ከአዲሶቹ ነፃነት ገብረመድህን እና ጋቶች ፓኖም አንፃር በምን መልኩ ቡድኑን ያገለግላል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ሆኗል። 

የእርስ በእርስ ግንኙነት 

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ 2-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ተስፋዬ ነጋሽ – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሤ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ 

ሄኖክ አየለ – አህመድ ሁሴን – ያሬድ ታደሰ

ወላይታ ድቻ (4-2-3-1)

መክብብ ደገፉ
 

አናጋው ባደግ –  አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – ያሬድ ዳዊት                

በረከት ወልዴ –  ጋቶች ፓኖም 

ፀጋዬ ብርሀኑ – እንድሪስ ሰዒድ – ቸርነት ጉግሳ

ቢኒያም ፍቅሬ     

© ሶከር ኢትዮጵያ