በባህር ዳር ከተማ አስተናጋጅነት የሚደረገውን የመጨረሻ ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።
ድል ካደረጉ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ያለፋቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ጎል አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ያሳዩትን መሻሻል በውጤት ለማሳጀብ እና ከአስጊው ቀጠና ለመራቅ ነገ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በፋሲል ከነማ አንድ ለምንም ተረተው ለዚህኛው ጨዋታ እየተዘጋጁ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና ከሊጉ መሪ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በስምንት ለማስቀጠል ድልን አልመው ጨዋታውን ይቀርባሉ።
በአሠልጣኝ ዘማርያም የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በጊዮርጊሱ ጨዋታ በእንቅስቃሴ ደረጃ እጅግ ተሻሎ ቀርቦ ነበር። በተለይም ግብ የማስተናገድ አባዜ ይዞት የነበረው የቡድኑ የኋላ መስመር እርጋታ በተሞላበት ሁኔታ የተጋጣሚን ቡድን አጥቂዎች ተቆጣጥሮ ሲጫወት ተስተውሏል። በተጨማሪም ቡድኑ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በመስመር በኩል በማፋጠን ተጋጣሚን ሲረብሽ ታይቷል። በዋናነት ደግሞ አስቻለው ግርማ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው ሩጫዎች ለተጋጣሚ አደጋን የሚያመጡ ነበሩ። ወደ መሐል ሜዳው ተጠግቶ መከላከል የሚያዘወትረው የቡና የተከላካይ መስመርም ነገ አስቻለውን ጨምሮ ሌሎች የቡድኑን የወገብ በላይ ተጫዋቾች በአግባቡ የማይቆጣጠር ከሆነ ከባድ ጊዜን ሊያሳልፍ ይችላል።
ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን ብቻ ያስተናገደው የቡድኑ የተከላካይ መስመር ለቡናዎች ከባድ ቢሆንም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ብቻ ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው የፊት መስመሩ መሻሻሎች ያስፈልጉታል። ከላይ እንደተጠቀሰውም በግል ብቃት ከሚገኙ አጋጣሚዎች ውጪ ቡድኑ በተደራጀ እና መደገም በሚችል መልኩ ጥቃቶችን ለመፍጠር ይቸገራል። ከዚህ መነሻነትም ቡናዎች የፊት መስመር ተጫዋቾቹን ፍጥነት የሚቆጣጠር ከሆነ ድሬዳዋ የማጥቂያ ሀሳብ ሊያጥረው ይችላል።
ብርትካናማዎቹ በነገው ጨዋታ የሱራፌል ጌታቸውን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኙም።
ከኳስ ጋር አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ ማሳለፍ ተቀዳሚ ምርጫው የሚያደርገው ኢትዮጵያ ቡና በነገውም ፍልሚያ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሱ አድርጎ እንደሚጫወት ይገመታል። በዋናነት ግን የአማካይ መስመሩ ላይ ያሉትን የተጫዋቾች የቴክኒክ ብቃት ተንተርሶ ከሚደረግ የመሐል ለመሐል ጥቃት በበለጠ ቡድኑ የመስመር ላይ አጨወቱን አስሎ ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል። በዚህም ለመከላከል ቅድሚያ ይሰጣል ተብሎ የሚገመተውን የድሬዳዋ የተከላካይ መስመር ለመዘርዘር በመስመር ላይ ያተኮሩ እንቅስቃሴዎችን ሊተገብር ይችላል።
የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የያዘው ቡና (አቡበከር) ከኳስ ጋር አስፈሪ ቢሆንም ከኳስ ውጪ ያለው አደረጃጀት ግን ጠጣርነት ይጎድለዋል። በተለይም ቡድኑ የሚያደርጋቸው ከማጥቃት ወደ መከላከል ሽግግሮች ጊዜያቸው የረዘመ ሲሆን ይታያል። ይህም ቡድኑን ለመልሶ ማጥቃት ሲያጋልጠው ይስተዋላል። ስለዚህም ነገ ድሬዳዋዎች ቡድኑ ከኋላ ኳስ ሲጀምር ተጭነው ለመቀበል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በአትኩሮት መጠበቅ ጠቀሜታን ሊያስገኝላቸው ይችላል።
አሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ በነገው ጨዋታ ጉዳት አጋጥሟቸው ከቡድኑ ጋር ልምምድ ያልሰሩትን ኃይሌ ገብረትንሳይ እና ታፈሰ ሰለሞንን የማያገኙ ይሆናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ17 ጊዜያት ያህል ተገናኝው ኢትዮጵያ ቡና 9 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ድሬዳዋ 3 ጊዜ ድል ቀንቶታል ፤ 5 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ 27 ጎሎች በኢትዮጵያ ቡና 14 ጎሎች ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ ተቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ፍሬው ጌታሁን
ዐወት ገብረሚካኤል – ያሬድ ዘውድነህ – ፍሬዘር ካሳ – ሄኖክ ኢሳይያስ
ዳንኤል ደምሴ – ሄኖክ ገምቴሳ
አስቻለው ግርማ – ሙኸዲን ሙሳ – ኢታሙና ኬይሙኒ
ጁኒያስ ናንጄቦ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
አቤል ማሞ
እያሱ ታምሩ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አሥራት ቱንጆ
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ረመዳን ናስር – ዊሊያም ሰለሞን
ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – አቤል ከበደ
© ሶከር ኢትዮጵያ