የአስር ሳምንት ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት ያመለጠውና ጎል በማስቆጠር ወደ ሜዳ የተመለሰው ስንታየሁ መንግሥቱ ስላሳለፈው አስቸጋሪ ጊዜ እና ቀጣዩ እቅዱ ይናገራል።
ከወላይታ ድቻ ታዳጊ ቡድን አድጎ በዋናው ቡድን መጫወት የቻለው ግዙፉ አጥቂ ወደ አርባምንጭ ከተማ አምርቶ የከፍተኛ ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ካጠናቀቀ በኋላ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ወደ ባህር ዳር ከተማ አምርቶ ሲጫወት ቆይቶ ዘንድሮ ወደ ጦና ንቦቹ ተመልሶ እየተጫወተ ይገኛል።
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እስከ አምስተኛ ሳምንት ድረስ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ጥሩ ጅማሮ አድርጎ የነበረው ስንታየው ከድሬደዋ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የጡንሻ መሳሳብ ጉዳት አስተናግዶ የአስር ሳምንታት ጨዋታዎች ለመራቅ ተገዶ ነበር። ተጫዋቹ ከጉዳቱ በማገገም ዛሬ ወላይታ ድቻ ከወልቂጤ ከተማ ባደረገው አስራ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ የገባ ሲሆን የድቻን ቀዳሚ ጎል በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር በጎል ወደ ሜዳ ተመልሷል።
ሶከር ኢትዮጵያ ስንታየሁን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ስላሳለፈው አስቸጋሪ ጊዜ እና የወደፊት እቅዱ አጭር ቆይታ አድርጓል።
” ጉዳቴ የጡንቻ መሳሳብ ነበር። በፍጥነት ከጉዳቴ እንዳላገግም ያደረገኝ በተለያዩ ጊዜያት አንድ ሁለት ሳምንት አርፌበት ከህመሜ ድኛለው ብዬ ከኳስ ጋር ልምምድ ስለጀምር በድጋሚ ጉዳቴ እያገረሸ ነው። ይህም ከሁለት ወር በላይ ከሜዳ እንድርቅ አድርጎኛል።
” ጎል ሳስቆጥር የተሰማኝ ደስታ ከፍተኛ ነበር። ምክንያቱ ረዥም ሳምንት ቡድኔን ማገልገል እየቻልኩ ሳላገለግል ቀርቼ ነበር። ዛሬ ከጉዳቴ አገግሜ ቡድኔን በማገልገሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከምንም በላይ ጎል በማስቆጠሬ ፈጣሪን አመሰግናለው።
” ከሜዳ መራቄ በብዙ ነገሮች ተፅዕኖ አድርጎብኛል። ዓመቱን ስጀምር ያቀድኩት ነገር ነበር። በጎል አግቢነቱ ከባለፉት ዓመታት በተሻለ በወጥነት ራሴን በጎል አግቢነት ፉክክር ውስጥ ማስገባት አስብ ነበር። ትንሽ ወደ ኃላ ሆኛለው። ያው ፈጣሪ የፈቀደው ነው የሚሆነው።
“በቀጣይ ተጨማሪ ጎሎች ስለማስቆጠር በሚገባ አስባለሁ። ፈጣሪ ይመስገን አሁን ጤናዬ ተመልሷል። ከዚህ በኃላ ጎሎችን በማስቆጠር ቡድኔንም በመጥቀምና አሁን ካሉኝ ጎሎች ከፍያለ የጎል መጠን ማድረስ እፈልጋለው። ይህንንም እንደማደርገውም ተስፋ አደርጋለሁ።
“ቡድናችን አሁን ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ነው። አሰልጣኛችን ዘላለም ሽፈራው ከመጣ በኃላ በመከባበር እና ሥራችን በአግባቡ በመሥራታችን እዚህ ደርሰናል። ከዚህም በኃላ የተሻለ ውጤት አስመዝግበን ጥሩ ደረጃ ይዘን የምንጨርስ ይሆናል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ