​ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሲዳማ ቡና

የነገ የሊጉ ውሎ የሚጀምርበትን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ እናስዳስሳችኋለን። 

ምንም እንኳን በተለያየ የውጤት ፅንፍ ላይ ቢገኙም ያለፉት ሳምንታት ጨዋታዎቻቸውን በሽንፈት የደመደሙት ሁለቱ ቡድኖች ለማገገም የሚረዳቸውን ወሳኝ ጨዋታ ነገ ያከናውናሉ። በባህር ዳር እና ድቻ ተከታታይ ሽንፈት የገጠማቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከዋንጫ ፉክክሩ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ ከመንሸራተት ለመዳን የነገው ውጤት አስፈላጊያቸው ነው። ከሆሳዕናም በላይ ግን አራት ተከታታይ ሽንፈት ላገኛቸው ሲዳማ ቡናዎች የነገው ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው በር ላይ ለመውጣት ካልሆነም ከበላያቸው ካሉት ክለቦች ጋር ተራርቀው ይበልጥ ጭንቀት ውስጥ እንዳይወድቁ አጥብቀው የሙሹት ነው። ይሁን እንጂ በማጥቃቱ ረገድ ደካማ ቁጥር ካላቸው ሦስት የሊጉ ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀሱት ሁለቱ ተጋጣሚዎች መገናኘት በገለልተኛ ተመልካቾች ዘንድ የጨዋታውን ተጠባቂነት ዝቅ ያደርገዋል።

ዘጠኝ ግቦች ብቻ በማስተናገዱ አሁንም በሊጉ የተሻለ የመከላከል ቁጥር ያለው ሀዲያ ሆሳዕና ከአጠቃላዩ 1/3ኛ የሚሆነውን የግብ መጠን በተሸነፈባቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎቹ ማስመዝገቡ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ በዚህ መልኩ መውረድ ነጥቦችን ለማጣቱ ምክንያት ሆኖ ቢነሳም ደካማው ግብ የማስቆጠር ሂደቱ መቀጠሉም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነጥብ ነው። በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ካስቆጠረ አስር ጨዋታዎች ያለፉት ሆሳዕና በእነዚሁ ጨዋታዎች የተጋጣሚን መረብ የደፈረው አራት ጊዜ ብቻ መሆኑ ይበልጥ የፊት መስመሩን ድክመት ያጋልጣል። 

እርግጥ ነው የነገው ጨዋታ በጥንቃቄ ከሚጀምርባቸው ጨዋታዎች ይልቅ ለማጥቃት ክፍት ሆኖ የሚያከናውነው ዓይነት ነው። ነገር ግን በተጠና አጨዋወት እና በድግግሞሽ የሚመጣው የፊት መስመር ስልነት በሆሳዕና ዘንድ እየታየ አይገኝም። ፊት መስመር ላይ በቁጥር ተመናምኖ የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ መገኘት እና ከእንቅስቃሴ ይልቅ ከቆሙ እና ከርቀት ከሚሞከሩ ኳሶች የተሻለ አስፈሪነት መላበሱ ግብ ቀላል እንዳይሆንለት አድርጓል። ተደጋጋሚ ዕድል የማያገኙት የቡድኑ አጥቂዎችም የቀደመ በራስ መተማመናቸው ላይ ሆነው አይታዩም።  ይህ ድክመታቸው ነገ የማይሻሻል ከሆነ ዳግም ከተከላካይ ክፍላቸው ጥንካሬ መነሻነት ተጥቦችን ለማሳካት ማለም የግድ የሚላቸው ይመስላል።

የአንድ ሳምንት ዕረፍት ያገኘው ሲዳማ ቡና እጅግ በርካታ ከሆኑት ዳካማ ጎኖቹ ጥቂቶቹን እንኳን ቀርፎ ለመምጣት ዕድል አግኝቷል። በሁለት ጊዜ ቻምፒዮኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ስር ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶችን አስተናግዶ በወረደ አቋሙ የቀጠለው ቡድኑ ከድል ጋር ከተገናኘ አምስት ጨዋታዎች አልፈዋል። በአዲሱ አሰልጣኙ ስር ከአንድ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ውጪ ሌላ ግብ ያላየው ሲዳማ በመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር ግብ የቀናው። ቡድኑን ከነገው ተጋጣሚው የሚለየው ነገር ቢኖር የተከላካይ መስመሩም እጅግ ድካማ መሆኑ ነው። በእነዚሁ ሰባት ጨዋታዎችም 11 ጊዜ ግብ አስተናግዷል። ከዚህ አንፃር ነገም የተጋጣሚው የማጥቃት ድክመት ተስፋ ይሰጠው እንደሆን እንጂ በአዲስ ተጫዋቾች ጭምር የተዋቀረው የተከላካይ ክፍሉ በዚህ ፍጥነት ተጠናክሮ መቅረቡ አጠራጣሪ ነው።

አዲስ ፈራሚው ዮናስ ገረመውን ከዳዊት ተፈራ በማጣመር የተደራጀው የቡድኑ የአማካይ ክፍል ወረቀት ላይ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አቅሙ ከፍ ያለ መስሎ ቢታይም አሁንም የውህደት ችግሩ ኃይል ከቀላቀለው የሀዲያ መሀል ክፍል ብርቱ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ያስገምታል። በተመሳሳይ ደካማ የውድድር ዓመት ቢያሳልፍም በሁለቱም አሰልጣኞች ተመራጭ የነበረው የሀብታሙ ገዛሀኝ አለመኖር ተጨምሮበት ይበልጥ ለአዲስ ፈራሚዎቹ ዕድል እንደሚሰጥ የሚጠበቀው አጥቂ መስመሩ የመጨረሻ ቅብብሎችን በስኬት ለመከወን እንዳይቸገር ያሰጋዋል።

በነገው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ቴዎድሮስ ታፈሰን በጉዳት  ሄኖክ አርፌጮን ደግሞ በግል ጉዳይ ምክንያት ሲያጣ ተስፋዬ አለባቸው እና አይዛክ ኢሲንዴንም በቅጣት አይኖሩም። አራቱም ተጫዋቾች የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ውስጥ ካላቸው ሚና አንፃርም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድናቸውን የቀደመ የመከላከል ትኩረቱን መልሶ እንዲያገኝ ለማድረግ አማራጮቻቸውን ያጠብባቸዋል። ሲዳማ ቡና በበኩሉ ፈቱዲን ጀማልን ከቅጣት መልስ ሲያገኝ በተቃኒው ሀብታሙ ገዛኸኝን በቅጣት ምክንያት መጠቀም አይችልም። ከዚህ ውጪ ዮሴፍ ዮሐንስ ፣ ይገዙ ቦጋለ እና ማማዱ ሲዲቤም ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት
                                                                               – ሁለቱ ቡድኖች በእስካሁኑ የሊጉ ቆይታቸው ሦስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አንድ አንድ ጊዜ ድል ሲቀናቸው አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ሀዲያ ሆሳዕና አራት ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚ ሲሆን ሲዳማ ቡና ሁለት ግቦች አሉት። 

ግምታዊ አሰላለፍ 

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

መሐመድ ሙንታሪ

ሱሌይማን ሀሚድ – አክሊሉ አያናው – ተስፋዬ በቀለ – መድሀኔ ብርሀኔ

ካሉሻ አልሀሰን – አዲስ ህንፃ – አማኑኤል ጎበና

ዱላ ሙላቱ – ዳዋ ሆቴሳ – ቢስማርክ አፒያ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ሽመልስ ተገኝ – ፈቱዲን ጀማል – ጊት ጋትኮች – መሀሪ መና

ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – ዮናስ ገረመው

ተመስገን በጅሮንድ –ያሬድ ከበደ – አዲሱ አቱላ


© ሶከር ኢትዮጵያ