ነገ ከሰዓት በሚከናወነው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ የቅርብ ተፎካካሪዎቹን በተከታታይ ጨዋታ ከረታ በኋላ ነገ በወራጅ ቀጠናው ያለው ጅማን ይግጠም እንጂ ውጤቱ ከተከታዮቹ ርቀቱን ከመጠበቅ አንፃር እንዳለፉት ሳምንታት ሁሉ ዋጋው ከፍ ያለ ነው። ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ ለማለት የሚችሉትን በማድረግ ላይ ለሚገኙት ጅማዎችም ከተጋጣሚያቸው ከባድነት አኳያ ጨዋታው ከፍ ያለ ግምት ቢሰጠውም ማሸነፍ እስትንፋሳቸውን ለማስቀጠል በጣሙን ያስፈልጋቸዋል።
ከቡድናቸው ጠንካራ ጎን በዘለለ አቀራረባቸውን ከተጋጣሚዎቻቸው አቅም አንፃር የሚቃኙት ፋሲሎች በነገው ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡናው አብዝተው ፊት መስመር ላይ ጫና ከፈጠሩበት የጨዋታ ዕቅድ የተለየ መልክ እንደሚኖራቸው ይታሰባል። ብዙ የመጫወቻ ቦታ ላይሰጣቸው የሚችለውን ተጋጣሚያቸውን ከመክፈት አንፃርም የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አማካዮቻቸውን ቁጥር አበርክተው ሊገቡ ይችላሉ። በቅብብሎች ሰብረው ለመግባት ከመሞከር ባለፈም ከመሀል የሚነሱ የተመጠኑ ኳሶችን ወደ ሙጂብ ቃሲም ማድረስ ሌላኛው አማራጫቸው ይሆናል። ግብ ወደ ማስቆጠሩ ከተመለሰው ግዙፉ አጥቂ በተጨማሪም የቡድኑ አማካዮች ለግብ ቀርበው መታየታቸው ግብ የሚያገኝበት አማራጩን ሰፊ ማድረጉ እንደነገው ዓይነት ጨዋታ ላይ ተጠቃሚ ያደርጋዋል። በዚህ ረገድ በቀኝ በኩል በሚያመዝነው የቡድኑ ጥቃት የሽመክት ጉግሳ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ስኬት ወሳኝ መሆኑ አይቀሬ ነው። በከባባድ ጨዋታዎች በጥንካሬው የቀጠነው የኋላ ክፍሉ ግን በመልሶ ማጥቃት ሊፈተን የሚችልበት ዕድል አይኖርም ማለት አይቻልም።
በትጋት ደረጃ የማይታማው ጅማ አባ ጅፋር ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጋር ተጨማሪ ስድስት ነጥቦችን ቢያሳካም ሙሉ ለሙሉ ወደ ውጤት መመለስ እንደተቸገረ ነው። ጥንቃቄ ተኮር መልክ እየተላበሰ የሚታየው ቡድኑ ፋሲልንም በተመሳሳይ መንገድ ለማቆም ሀሳቡ እንደሚኖረው ቢታሰብም ከስህተቶች አለመፅዳቱ ግን ዳግም ግብ እንዲቆጠርበት ሊያደርገው ይችላል። ያም ቢሆን በጨዋታዎች መሀል ብልጭ የሚለው በፈጣን ሽግግር ግብ አፋፍ የሚደርስበት አካኋን ከነገ ተጋጣሚው ለመሀል ሜዳ የሚቀርብ የተከላካይ ክፍል አንፃር ውጤት ሊያስገኝለት ይችላል። ወደ ኋላ 10 ጨዋታዎችን ብንመልስ እንኳን በአንድ ጨዋታ ብቻ ግብ እምቢ ያለው ጅማ ነገም በነተመስገን ደረሰ አጨራረስ የፋሲልን በር ለማንኳኳት ግምት ቢሰጠው አያስገርምም። ሆኖም ከአቡበከር ኑሪ ድንቅ ብቃት በተጨማሪ የሜዳ ላይ ተሰላፊዎቹን ትኩረት በአግባቡ መሰብሰብ ካልቻለ እና ለፋሲል ቅብብሎች ክፍተት ከሰጠ አስቆጥሮም ሽንፈት ሊያገኘው የግድ ይሆናል።
በነገው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ሀብታሙ ተከስተን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ከማጣቱ በቀሪ ቀሪ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ነው። ወንድምአገኝ ማርቆስን ከቅጣት መልስ በሚያገኘው ጅማ አባ ጅፋር በኩልም ከከድር ኸይረዲን ጉዳት ውጪ ሌሎቹ ተጫዋቾች ዝግጁ ሲሆኑ አዲስ ፈራሚዎቹ አሌክስ አሙዙ እና ራሂም ኦስማኖም በቡድን ዝርዝሩ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉበት ዕድል አለ።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ በሊጉ የአምስት ጊዜ የግንኙነት ታሪክ ሲኖራቸው ፋሲል ከነማ ሦስት ጊዜ አሸንፎ በሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል ፤ ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን በፋሲል ላይ ድል አልቀናውም። በጨዋታዎቹ ፋሲል 11 ጅማ 2 ግቦችን አስመዝግበዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኬ
እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው
ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ
ሙጂብ ቃሲም
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
አቡበከር ኑሪ
ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኤልያስ አታሮ
ንጋቱ ገብረሥላሴ – አማኑኤል ተሾመ – ሙሉቀን ታሪኩ
ተመስገን ደረሰ – ሳዲቅ ሴቾ – ሱራፌል ዐወል
© ሶከር ኢትዮጵያ