ፋሲል ከነማ እና ጅማ አባጅፋርን ያገናኘው የዘጠኝ ሰዓቱ ጨዋታ በፋሲል 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለምንም ረተው ለዚህኛው ጨዋታ የቀረቡት የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማዎች በአምስት ቢጫ ምክንያት ቅጣት ላይ የሚገኘውን ሀብታሙ ተከስተን ብቻ በይሁን እንዳሻው ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እየጣሩ የሚገኙት ጅማ አባጅፋሮች በበኩላቸው በወልቂጤ ከተማ ሁለት ለአንድ ከተሸነፉበት ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም አብርሀም ታምራት እና ሳዲቅ ሴቾን በሀብታሙ ንጉሴ እና ሙሉቀን ታሪኩ ተክተዋል።
ጨዋታውን በጥሩ ንቃት የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች በሦስኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ወደ ጎል በላከው ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ከአንድ ደቂቃ በኋላም በዛብህ መለዩ ሌላ ጥሩ ኳስ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ወጣቱ የግብ ዘብ አቡበከር ኑሪ አምክኖበታል። በድጋሜ በዘጠነኛው ደቂቃም ሙጂብ ቃሲም በተከላካዮች መሐል የተሰነጠቀለትን ኳስ መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥሮ አቡበከር በጥሩ ቅልጥፍና አድኖበታል።
ጨዋታው የከበዳቸው ጅማ አባጅፋሮች ከ14ኛው ደቂቃ ጀምሮ ግን እጅ መስጠት ጀምረዋል። በዚህ ደቂቃም ሙጂብ ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ ወደ ጎል የመታው ኳስ የግቡ ቋሚን ገጭቶ ሲመለስ በድጋሜ ወደ ጎል በመምታት ኳስን ከመረብ አዋህዷል። ግብ ማስቆጠራቸው ተጭኖ ከመጫወት ያልገደባቸው ፋሲሎች ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ተጨማሪ ጎል አግኝተዋል። በዚህም ሙጂብ ቃሲም ከቀኝ መስመር እንየው ካሳሁን ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብነት ቀይሯል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም የጠራ የግብ ማግባት ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ጅማ አባጅፋሮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችላቸውን ግብ ለማግኘት ተቸግረው ታይተዋል። ፋሲሎች በአንፃሩ ሁለተኛውን ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ሲሰነዝሩት የነበሩትን የሰላ ጥቃት ቀነስ አድርገው ተጫውተዋል። አጋማሹም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በፋሲል መሪነት ተጠናቋል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የጅማን የግብ ክልል መጎብኘት የያዙት ፋሲሎች ገና አጋማሹ በተጀመረ በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ በሱራፌል አማካኝነት ወደ ግብ የላኩት ኳስ የጎል አግዳሚ መልሶባቸዋል። ይህንን አደገኛ ሙከራ ያደረገው ሱራፌል በ56ኛው ደቂቃ የተገኘውን የቅጣት ምት አሻምቶ ሽመክት ሦስተኛ ጎል ለማስቆጠር ጥሮ ነበር። በአንፃራዊነት በዚህኛው አጋማሽ ተሽለው የታዩት ጅማዎች ተከታታይ የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። ነገርግን ቡድኑ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ደርሶ ግብ ማስቆጠር እጅግ ፈተና ሆኖበት ታይቷል።
ጨዋታው የቀለላቸው ፋሲሎች አሁንም የግብ ማስቆጠር ፍላጎታቸው ሳይጠፋ በ78ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ለማስፋት ዳድተዋል። በዚህ ደቂቃም ሽመክት ከመዓዘን ያሻገረውን ኳስ በረከትን ለውጦ ወደ ሜዳ የገባው ፍቃዱ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ አብዱልከሪም ይዞበታል። ቡድኑም በጥሩ ሁኔታ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ጨዋታውን ፈፅሟል። ጅማዎችም ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈታቸውን አስተናግደው ከሜዳው ወጥተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት ፋሲል ከነማዎች ነጥባቸውን 38 በማድረስ ነገ ጨዋታ ካለው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ 11 አሳድገዋል። በተቃራኒው በጨዋታው እጅግ ደክመው የታዩት ጅማዎች ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ሳይችሉ በሰበሰቧቸው 10 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ