በኬንያዊው ፓትሪክ ማታሲ እንቅስቃሴ ደስተኛ ያልሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አዲስ የግብ ዘብ ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ እየተመለከቱ ይገኛሉ።
የውጪ ዜጋ ግብ ጠባቂዎችን በማስፈረም የሚታወቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 2011 ላይ ፓትሪክ ማታሲን በማስፈረም ግባቸውን ሲያስጠብቁ መቆየታቸው ይታወሳል። የዘንድሮውን ውድድርም በቋሚነት የጀመረው ማታሲ እስካሁን ክለቡ ግልፅ ባላደረገው ምክንያት ከስብስቡ ርቆ አዲስ አበባ ይገኛል። እርሱ ከስብስቡ ከራቀ በኋላም አሠልጣኝ ማሒር ዴቪድስ ለዓለም እና ባሕሩን በመጠቀም ሲጫወቱ ቆይተዋል።
ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘው መረጃ ከሆነ ክለቡ ጀምስ አሊቶ የተባለ ዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም የሙከራ ጊዜ እንደሰጠ ታውቋል። ለቫይፐርስ፣ ዩ አር ኤ ኤፍ ሲ እና ዛናኮ የተጫወተው አሊቶ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከቡደኑ ጋር ልምምድ እየሠራ ረጅም ቀናት ተቆጥረዋል።
ጀምስ አሊቶ ለቡድኑ ፊርማውን የሚያኖር ከሆነ ከካሊሲቡላ ሀኒንግተን፣ ሮበርት ኦዶንካራ እና ዴኒስ ኦኒያንጎ በመቀጠል አራተኛው የፈረሰኞቹን መለያ የለበሰ ዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ