​የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 2-0 ጅማ አባ ጅፋር 

የፋሲል እና የጅማ አሰልጣኞች ጨዋታውን አስመልክቶ ለሱፐር ስፖርት ኃሳባቸውን እንዲህ አካፍለዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለባህር ዳር ውጤታቸው

አንድ ጨዋታ ነው ዕኩል ለዕኩል የወጣነው ፤ ከአምስት ጨዋታ አራቱን አሸንፈናል። አሁን የሊግ አመራራችን ጥሩ በራስ መተማመን የሚሰጥ ነው። ቀጣዩ የዕረፍት ጊዜም በመንፈስም በአካልም የምንዘጋጅበት ጥሩ ጊዜ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ስለሚወሰድባቸው ብልጫ

እሱን ማረም አለብን። ፍላጎቴ እንደዛ አይደለም። ነገር ግን አንዳንዴ ተጫዋቾች 2-0ን እንደሰፊ ውጤት በመውሰድ ራሳቸውን 100% ከመስጠት ቆጠብ አድርገዋል። ያ ደግሞ ትንሽ ዋጋ ያስከፍላል። ወደ ፊት የሚታረም ቢሆንም አጠቃላይ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረግነው ነገር መልካም ነው። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተቆራረጡ ስህተቶች አሉ። ዋናው ግን ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ፍላጎት ነበረን ፤ ተሳክቶልናል። መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።

ስለቡድኑ የእስካሁኑ ጠንካራ ጎን

አንደኛ የኳስ ቁጥጥሮች እየተሻሻሉ ሄደዋል። ሁለተኛ እንደቡድን የመከላከል ብቃታችን ጥሩ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ተቃራኒ ሜዳ ገብተን የምናደርጋቸው ሙከራዎች በጣም ጥሩ ናቸው። እንደዛም ሆኖ የምንስታቸው አሉ። ለምሳሌ በመጀመሪያው አጋማሽ 3-0 ማረፍ እንችል ነበር። እንደነበረከት ያገኙትን ለመጨረሰ 100% ትኩረት ማድረግ አለባቸው። እነዚህ ነገሮች የሚሻሻሉ ቢሆንም በቡድኑ ላይ ግን ከፍተኛ ለውጦች ናቸው ብዬ አስባለሁ።

ስለባህር ዳር ቆይታቸው

የባህር ዳር ቆይታችን በጣም ደስ ይላል። ባህር ዳር ላይ በርካታ የፋሲል ደጋፊዎች አሉ ፤ ከጎንደርም ከዚህም። ሁል ጊዜም ከጨዋታ በኋላ ከስታድየም ሆቴል አምስት ደቂቃ የሚፈጅ መንገድ አንድ ሰዓት ነው የሚፈጀው። የህዝቡ ድጋፍ ለእኛ ትልቅ ስንቅ ነው። እና ለመላው የፋሲል ደጋፊዎች እስካለንበት ደረጃ ድረስ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። 

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባ ጅፋር 

ስለጨዋታው

የፋሲል ትልቁ ጠንካራ ጎን የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች በተጋጣሚ ላይ ጫና በመፍጠር ነው ብዙ ጊዜ የሚጫወቱት። ይህንን ለተጫዋቾቹ ነግሬያቸው ነበር። ከ20 ደቂቃ በኋላ ኳሱን እየተቆጣጠርነው በአካልም በአዕምሮም ተቀይረን ወደ ጨዋታው ምት እንገባለን የሚል ሀሳብ ነበረን። ግን ካላቸው የተጫዋች ጥራት በጎል አዳኙ ሙጁብ ቃሲም አማካይነት ሁለት ጎሎች አስቆጥረውብናል። ባልተጠበቀ ሰዓት ነው ፤ እነዚህን ደቂቃዎች ብናልፍ ኖሮ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ እንችል ነበር። ዞሮ ዞሮ በእኛ በኩል አብዛኞቹ ጉዳት ላይ ነው ያሉት። ውብሸት እና አማኑኤል በጉዳት ነው የገቡት ብዙአየሁም ጉዳት ላይ ነው። በእንቅስቃሴም የተጎዱ ተጫዋቾች አሉ። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በተወሰኑ ተጫዋቾች ነው ለመጫወት የሞከርነው ፤ ካለን የተጫዋች ስብስብ አንፃር ማለት ነው። እንግዲህ ምንም ማድረግ አይቻልም በዕረፍት ሰዓታችን ሰርተን ፣ አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርመን ለቀጣይ ጨዋታዎች እንዘጋጃለን። 

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የነበራቸው መነቃቃት ከመጀመሪያው ስላልነበረበት ምክንያት

የመጀመሪያውን 20 ደቂቃ ተጭነውን ተጫውተዋል። በጎል ነው የቀድሙን። ባልተጠበቀ ሰዓት ስላገቡብን በእኛ ቡድን ላይ የመበታተን ነገር ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የእነሱን ተቃራኒ አጨዋወት ነው ይዘን የገባነው። ፈጣኖች ስለሆኑ እና ረጃጅም ኳሶች ስለሚጫወቱ ኳሱን በቅርበት እንዲቀባበሉ ነበር የነገርኳቸው እና ያንን ሜዳ ላይ አድርገውታል። በዚህ አምስት ጨዋታዎች ሳይ ግን ተጫዋቾቹ በሜዳ ላይ ማድረግ የሚገባቸውን የሚቻላቸውን ነገር አድርገዋል። ዞሮ ዞሮ በሥራ ከተጠመድን አሁን ያሉን ዕድሎች ብዙ የከፉ አይደሉም። ተጫዋቾቼ ግን አቅማቸው የፈቀደውን ስላደረጉ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ