“ነገ የተሻለውን አማኑኤል ለመፍጠር ተግቼ እየሠራሁ እገኛለሁ” – አማኑኤል ጎበና

ሀድያ ሆሳዕና የባህር ዳር ቆይታውን ሲዳማ ቡናን በመርታት በድል ካጠናቀቀ በኋላ ከቡድኑ ቁልፍ አማካይ አማኑኤል ጎበና ጋር ቆይታ አድርገናል።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍነው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ከተረቱበት ጨዋታ ውጭ በአስራ አምስቱም ጨዋታዎች ሀድያ ሆሳዕናን በመጀመርያ ተሰላፊነት አገልግሏል። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በየጨዋታው ይዘውት የሚገቡትን ታክቲክ ከሚተገብሩ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከልም አማኑኤል ጎበና አንዱ ነው። በዛሬው ዕለት የቡድኑን እንቅስቃሴ ከተከላካይ ፊት በመሆን ሲመራ እና ሲያደራጅ የዋለው አማካዩ ስለ ውድድር ዓመቱ እና በሀዲያ ሆሳዕና እያሳለፈ ስለሚገኘው ጥሩ እንቅስቃሴ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ስለዛሬው ጨዋታ

“የዛሬው ጨዋታ በጣም ጥሩ ነበር። ያው እኛ ከሁለት ጨዋታ ሽንፈት ነበር የመጣነው፤ ለዛም የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ነበር የተነጋገርነው። እነሱም ከሽንፈት እንደመምጣታቸው ጠንካራ ቡድን እንደሚገጥመን አስበን ነበር። ሜዳ ላይ እኛ የተሻለ የማሸነፍ ፍላጎት ስለነበረን ጨዋታውን አሸንፈን ወጥተናል።”

የቡድኑ አደረጃጀት ላይ እየተወጣ ስለሚገኘው ሚና

“ቡድናችን በመከላከሉ ሆነ በማጥቃቱ ረገድ እንደ ቡድን ነው የምንቀሳቀሰው። ብዙ ጊዜ ግቦች በቀላሉ አይቆጠርብንም። በዛሬው ጨዋታ ከሌላው ጊዜ በተለየ በተከላካይ አማካይነት በደንብ ብቻዬን እንድጫወት ነበር ኃላፊነት የተሰጠኝ። ያንንም ከተከላካዮች ፊት ሆኜ በሚገባ ተወጥቻለው ብዬ አስባለሁ። አሰልጣኙ የሰጠኝ የጨዋታ ሚና እና ወደ ሜዳ ከመግባቴ በፊት የነገረኝ ነገር ይበልጥ አግዞኛል ብዬ አስባለሁ።”

ቡድኑ አዳዲስ ስላመጣቸው አማካይ ተጫዋቾች እና በቀጣይ ለተሰላፊነት ስለሚገጥመው ፈተና

“ይህ ይሆናል ብዬ አልገምትም። እስካሁን በነበሩት ጨዋታዎች በተቻለኝ መጠን ቡድኑን እያገለገልኩ እገኛለሁ። በባለፈው የባህር ዳር ጨዋታ ብቻ በህመም ቡድኑን ማገልገል ሳልችል ቀርቻለሁ። ያለኝን አቅም ይበልጥ አጎልብቼ የተሻለ ነገር ለመስራት አልማለሁ። ከዛ ውጭ የሚጠጥሙኝን ፈተናዎች ጠንክሬ በመስራት እወጣዋለሁ ብዬ አስባለሁ።”

ሆሳዕና አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ይገኛል?

“አዎ በትክክል! ገና የሚቀሩ ዘጠኝ ጨዋታዎች አሉ። በዚህ ሒደት የሚፈጠረው ነገር አይታወቅም። ዋናው ነገር እኛ የሚጠበቅብንን እያደረግን ጨዋታዎችን እያሸነፍን መቀጠል ነው። ከዛ ውጭ እያንዳንዱን ጨዋታ እያሸነፍን በመቀጠል ልዮነቱን አጥበን በዋንጫ ፉክክር መቀጠል እንደምንችል እንረዳለን።”

እያሳየው ከሚገኘው አቋም አንፃር በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ስላለመካተቱ

“ያው የእኔ በፊት የነበረኝ አቅም ይታወቃል። አሁን ላይ ደግሞ ይበልጥ ተሻሽዬ መጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ። በቀጣይ ከዚህ በላይ በመሻሻል ዋነኛው አላማዬ። ዘንድሮ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ እገኛለሁ፤ ይሄን ማስቀጠል ዋነኛ እቅዴ ነው። የብሔራዊ ቡድን ምርጫ ብዙ ጊዜ የአሰልጣኞች ነው፤ አሰልጣኞች የተመቻቸውን እና ባዩት መሠረት ለሚፈልጉት አጨዋወት ይሆነኛል የሚሉትን ሰው ይመርጣሉ፤ በእሱ ላይ ችግር የለብኝም። እንደ ማንኛውም ተጫዋች ብመረጥ እና ሀገሬን ባገለግል ግን ደስ ይለኛል ምርጫውን ለአሰልጣኞች ትቼ እኔ ግን ዛሬ ላይ ካለው አማኑኤል ነገ የተሻለውን አማኑኤል ለመፍጠር ተግቼ እየሰራሁ እገኛለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ