​የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ለሱፐር ስፖርት አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ስለውጤቱ እና ስለተጫዋቾቻቸው

ውጤቱ በጣም ጥሩ ነው ለእኛ። ተጋጣሚያችን እንደሚታወቀው በጣም ጠንካራ ነው። እንቅስቃሴያችን ከዚህ ቀደም ከነበረው እየቀነሰ ነው የመጣው። ቢሆንም ግን ወጣት ተጫዋቾች ስለሆኑ እና በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ጫና ስለሚኖርባቸው እንዲሁም ስኳዳችን ትንሽ ጠበብ ስላለ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው።

በቶሎ ግብ ማስቆጠራቸው ስለነበረው ተፅዕኖ

በእርግጥ እኛ ብዙ ጊዜ ከምንጫወተው ዛሬ ለየት ያለው ኳስ ይዘን ለመጫወት ሞክረን ነበር። ያው ተደጋጋሚ ልምምዶች ስለሚያስፈልጉት በራስ መተማመን ያስፈልጋል። ተቃራኒ ቡድን ደግሞ እንደሚታወቀው በጣም ጠንካራ ነው። እና ካሰብነው ትንሽ ለወጥ አደረግነው። ቢሆንም ግን ጥሩ ነው።

ውጤታቸው ከሦስቱ አስተናጋጅ ከተሞች አንፃር

በእርግጥ በውጤት ከታየ ጅማ ላይ የወሰድነው ጥሩ ነጥብ ነው። አዲስ አበባ ላይ ሰባት ፣ እዚህ ሁለት ነጥብ ነው የወሰድነው። በእርግጥ ተጋጣሚዎቻችን እዚህ ሜዳም ጠንካሮች ነበሩ እና ክፍተቶችም አሉብን። በቀጣይ ጊዜያት ደግሞ በተጫዋቾችም በልምምዶችም አሟልተን ለመምጣት ነው ሀሳባችን።

አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

በጣም ጥሩ ነገር ነበርን። ጎል አስቆጥረናል ፣ ንፁህ የማግባት ዕድሎችንም ፈጥረናል። ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዕድሎቻችንን ብናስቆጥር ጨዋታውን መጨረስ እንችል ነበር። በመጀመራያው አጋማሽ ማብቂያ ላይ ጠንክረውብን ነበር። ግን እንዳገኘናቸው ዕድሎች ቁጥር ብዛት እንዴት እንዳላስቆጠርን አላውቅም።

በባህር ዳር ስለነበረባቸው ድክመት

በጨዋታ ረገድ ጥሩ ነበርን። ጨዋታዎችን መግደል ላይ ነበር ድክመታችን። የዛሬው  ጨዋታ አንዱ ምሳሌ ነው። ወደ ፋሲሉ ጨዋታም ብትሄድ ማሸነፍ የምንችልባቸው ዕድሎች ኖረው በሽንፈት ጨርሰናል። ከድሬዳዋ ጋርም እንዲሁ ዕድሎች ኖረውን ነጥብ ተጋርተናል። ዛሬም ሁለት ሦስት ያለቀላቸው አጋጣሚዎች ነበሩን ፤ ግን አላደረግነውም። በመጨረሻም ነጥብ ተጋርተናል። 

ስለቻምፒዮንነት ስለማሰባቸው

በሂሳብ ስሌት እስከተቻለ ድረስ ጉዟችንን እንቀጥላለን። ተስፋ አንቆርጥም እንታገላለን ፤ ምንም ሊፈጠር ይችላል።

አዲስ ግብ ጠባቂ ስለማሰባቸው

አሁን ባለው ሁኔታ በባህሩ በጣም ደስተኛ ነን። ዕድሉን ማግኘት በቻለበት አጋጣሚ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ነው። በዚሁ እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን። 


© ሶከር ኢትዮጵያ