ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ቀዝቃዛው ጨዋታ በጌዲኦ ዲላ አሸናፊነት ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አስራ ስድስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ጌዲኦ ዲላ እና አዲስ አበባ ከተማን አገናኝቶ በአሰልቺ እንቅሴቃሴ ታጅቦ በጌዲኦ ዲላ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የጨዋታው ፊሽካ ከተሰማበት ደቂቃ አንስቶ እስከ ፍፃሜው ድረስ የሚባክኑ ረጃጅም ኳሶች የበዙበት አልፎም ለዕይታ ሳቢ ያልነበረ አጨዋወት የተመለከትንበት ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መሀል ሜዳ ላይ በይበልጥ ባመዘነው እና በኃላ ላይ በረጃጅሙ ወደ መስመር ኳሶችን በመጣል ቡድኖቹ ለማጥቃት ያላቸውን ኃይል ለመጠቀም ጥረት ቢያደርጉም የሚያሳዩት ደካማ የጨዋታ መንገድ የተለየ ነገርን እንዳንመለከት ዳርጎን ተስተውሏል፡፡

የጠሩ ሙከራዎችን መደበኛው የመጀመሪያ አርባ አምስት እስኪጠናቀቅ መመልከት ሳንችል ቀርተን በጭማሪው የዕረፍት መገባደጃ ሰአት ጌዲኦ ዲላዎች ግብ አግኝተዋል። አዲስ አበባ ከተማዎች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግራ ካደላ ቦታ ከግብ ክልሉ ጠርዝ እፀገነት ግርማ አክርራ ወደ ጎል ስትመታ የአዲስ አበባ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ቤተልሄም ዮሐንስ በቀላሉ መያዝ የምትችለውን ኳስ መቆጣጠር ባለመቻሏ የሰራችሁን ጉልህ ስህተት ተጠቅማ ተከላካይዋ ማርያም ታደሰ በፍጥነት የተተፋውን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጣው ክለቧን 1ለ0 አድርጋ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ጨዋታው አሰልቺነቱ እንዳለ ሆኖ ቢቀጥልም በአንፃራዊነት በሙከራ ረገድ ግን አዲስ አበባ ከተማዎች ተሽለው የታዩበት ነበር፡፡በይበልጥ ረጃጅም ኳሶች በርክተው ማየት በቻልንበት በዚህኛው አጋማሽ 56ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ከተማዋ አምበል ሩታ ያደታ ከርቀት ያደረገቻት ሙከራ እና ሰለማዊት ኃይሌ ከመስመር በኩል 60ኛው ደቂቃ ላይ የመጣላትን ኳስ አስቆጠረች ሲባል ካመከነችው አጋጣሚ ውጪ የተለየ ነገርን መመልከት ሳንችል ከአጀማመሩ እስከ ፍፃሜው አሰልቺ የነበረው ጨዋታ 1ለ0 በጌዲኦ ዲላ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ