​ካፍ አዲስ ፕሬዝዳንት መርጧል

በውዝግብ እና በሴራ ንድፈ ሀሳብ የተሞላው የካፍ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በዶ/ር ፓትሪስ ሞሴፔ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከአራት ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ምርጫ አህመድ አህመድን በፕሬዝዳንትነት የሾመው የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ ጠባቂ ካፍ ከማዳጋስካራዊው አወዛጋቢ የሥልጣን ቆይታ በኋላ ዛሬ አዲሱን መሪውን አግኝቷል። ሞሮኮ ራባት ላይ እየተከናወነ በነበረው 43ኛው የተቋሙ ጠቅላላ ጉባዔ ከደቂቃዎች በፊት ይፋ በተደረገው የምርጫው ውጤትም ዶ/ር ፓትሪስ ሞሴፔ 8ኛው የካፍ ፕሬዝደንት በመሆን የመጀመሪያው ደቡብ አፍሪካዊ ሆነዋል።

የ59 ዓመቱ ባለፀጋ በ 2.9 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሀብታቸው በአህጉሪቷ የባለፀጎች ዝርዝር ላይ ዘጠነኛ ደረጃን ይዘዋል። የአፍሪካ እግርኳስ በጎ ነገሮች ላይ በማተኮር በዓለም ምርጡ እንዲሆን መስራት ዓላማቸው መሆኑ የምርጫ ቅስቀሳ መሪ ቃላቸው የነበረው አዲሱ ፕሬዝዳንት ከስፖርቱ ጋር ጥብቅ ቁርኝትም አላቸው። በዚህም የሀገራቸው ደቡብ አፍሪካው ማማሎዲ ሳንዳውንስ ባለቤትነት መሆናቸው ይታወቃል። ክለቡ በታሪኩ ካገኛቸው 10 ክብሮችም ሰባቱን አብረው ያጣጣሙት ዶ/ር ፓትሪስ ሞሴፔ “የእኔን ያህል በአፍሪካ እግርኳስ ላይ ኢንቨስት ያደረገ የለም ፤ ለእግርኳስ ያለኝ ፍቅር የለክፍት ያህል ነው።” ይላሉ። አዲሱ አለቃ በብዙ ምስቅልቅል ውስጥ ሆኖ የሚረከቡትን ተቋም በቀጣይ ዓመታት እንደሀብታቸው ከፍ ያደርጉት እንደሆነም ይጠበቃል። 

 
በተያያዘ ዜና በምርጫው ሌሎች ተፎካካሪዎች የነበሩት የሴኔጋሉ ኦገስቲን ሴንጎር እና የሞሪታኒያው አህመድ ያህያም የዶ/ሩ ምክትል ሆነው ካፍን እንደሚያስተዳድሩ ታውቋል።