​ኢትዮጵያ የሴካፋ ዋንጫን ታዘጋጃለች

የክፍለ አህጉሩን የዘንድሮ ውድድር ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ እሺታዋን መስጠቷ ታውቋል።

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግርኳስ ማህበራት ካውንስል በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በሁለቱ ፆታዎች አምስት ውድድሮችን የሚያከናውን ይሆናል። ከእነዚህ ውስጥም የወንዶቹን የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ አዘጋጅነት ኢትዮጵያ እንደወሰደች ተሰምቷል። በሞሮኮ ራባት ከተካሄደው የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ አስቀድሞ  በከተማዋ በሚገኘው ሶፊቴል ሆቴል በተደረገው የተቋሙ ስብስባ ላይ ነበር የኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ውሳኔ ያገኘው።

በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት አምና ሁለት ውድድሮችን ብቻ ለማድረግ የተገደደው ሴካፋ የዘንድሮውን ውድድር መጀመሪያ ቀን ይፋ ባያደርግም ተካፋይ ሀገራት በ 23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖቻቸው እንደሚወዳደሩ ታውቋል።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በ1980 ፣ 1997 ፣ 1999 ፣ እና 2008 ውድድሩን ስታዘጋጅ ዩጋንዳ ደግሞ 14 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚ ናት።

© ሶከር ኢትዮጵያ