“ብዙም የተለወጠ ነገር አላየሁም” – ጋቶች ፓኖም

ከኢትዮጵያ ውጭ የዓመታት ቆይታ በኃላ ወደ ሀገሩ በመመለስ በወላይታ ድቻ ጥሩ ጅማሮ እያሳየ የሚገኘው ጋቶች ፓኖም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ አጭር ቆይታ አድርጓል።

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ራሱን በማሰተዋወቅ ወደ ሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ አምርቶ ብዙም ቆይታን ሳያደርግ ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሶ በመቐለ 70 እንደርታ የስድስት ወራት ቆይታ አድርጓል። ዳግመኛ በግብፆቹ ኤል ጎውና እና ሀራስ ኤል ሁዳድ እንዲሁም ወደ ሳውዲ አረቢያ ዲቪዥን ሁለት ክለብ አል-አንዋር አምርቶ መጫወቱም ይታወቃል።

ለዓመታት ከኢትዮጵያ እግርኳስ የራቀው ጋቶች ዳግመኛ ወደ ሀገሩ በመመለስ በቅርቡ ለወላይታ ድቻ በመፈረም የሁለት ሳምንት ጨዋታዎችን የመጀመርያ አሰላለፍ በመግባት ጥሩ ጅማሮ እያደረገ ይገኛል። በመጀመርያ ጨዋታው ቡድኑን ባለድል ያደረገች ጎል አዳማ ከተማ ላይ ያስቆጠረው ጋቶች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ሊጉ ብዙም ሳይለወጥ እንደጠበቀው ተናግሯል። ” በሊጉ ዙርያ ብዙም የተለወጠ ነገር አላየሁም። ጨዋታዎቹ በዲኤስ ቲቪ በቀጥታ መተላለፋቸው እና ውድድሩ እንደ ቶርናመት በአንድ ቦታ መካሄዱ እንጂ በእንቅስቃሴ ሜዳው ውስጥ የተለየ ነገር አልተመለከትኩም። ሁሉም ነገር ያው ነው። ከኢትዮጵያ ሊግ ትንሽ በመራቄ ተለውጦ የጠበቀኝ ነገር አላየሁም።”

ከተለያዩ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ ቆይቶ ወላይታ ድቻን የተቀላቀለው አማካዩ አንዳንድ ክለቦች የዝውውረሰ ጥያቄ ቢያቀርቡም ከአሰልጣኝ ዘላለም ጋር በቅድሚያ የተነጋገሩ በመሆኑ የጦና ንቦቹን ምርጫው ማድረጉን ገልጿል። ” ወላይታ ድቻ መጀመርያ አካባቢ የነበረበት ደረጃ ጥሩ አልነበረም። አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል። የቡድኑም አጨዋወት በጣም ተመችቶኛል። በቀጣይም ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እንደ ቡድን እናስባለን።” ሲልም ከቡድኑ ጋር ያለውን ጅማሮ እንወደደው ተናግሯል።

በ2010 በመቐለ ለስድስት ወራት ካደረገው ቆይታ ውጪ ያለፉትን አራት ዓመታት በውጪ ሀገራት የቆየው ጋቶች በቀጣዩ ዓመት ተመሌሶ ከሀገር ውጪ ስለመጫወት እንደሚያስብ ተናግሯል። ” ከወላይታ ድቻ ጋር ይሄን ዓመት ብቻ ነው የማገለግለው። በቀጣይ ዓመት ከኢትዮጵያ ውጭ ወጥቶ የመጫወት ዕቅዶች አሉኝ። የተጀመሩ ፕሮሰሶች አሉ፤ ይሳካሉ ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።” ሲል ሀሳቡን አጋርቷል።

ጋቶች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የነበረውን አጭር ቆይታ ያጠናቀቀው ወደ ዋልያዎቹ የመመለስ ዕቅዱን በመግለፅ ነው። “ከብሔራዊ ቡድን እየራቅሁ እንደሆነ አስባለሁ። ያው ዓምና ኮሮናም የነበረ በመሆኑ ጨዋታዎችን አላደረኩም። አሁን ወደ እንቅስቃሴ ገብቻለው በቀጣይ ለመመለስ አስባለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ