ሪፖርት | ቡናማዎቹ ቡርትካናማዎቹን አሸንፈዋል

በባህር ዳር ከተማ የተደረገው የመጨረሻ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተቋጭቷል።

በአስራ አምስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ የተለያዩት ድሬዳዋዎች አንድ ነጥብ ካገኙበት ጨዋታ ሱራፌል ጌታቸውን ብቻ በሄኖክ ገምቴሳ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ አንድ ለምንም ተሸንፈው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ታፈሰ ሰለሞን እና አማኑኤል ዮሃንስን በፍቅረየሱስ ተክለብርሃን እና እያሱ ታምሩ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታውን በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ገና ሁለት ደቂቃ ሳይሞላ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አቡበከር ናስር ከዊሊያም ሠለሞን የደረሰውን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ለተቆጠረባቸው ጎል ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያላመነቱት ድሬዳዋ ከተማዎች ግቡን ካስተናገዱ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ጁንያስ ናንጄቦ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ መረብ ላይ ባሳረፈው ኳስ አቻ ሆነዋል።

በፈጣን እንቅስቃሴዎች ታጅበው ሁለት ጎሎችን ያስመለከቱት የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በድጋሜ በ5ኛው እና በ6ኛው ደቂቃ የግቦቹ ባለቤቶች በሆኑት አቡበከር እና ናንጄቦ ሌላ ጥቃት ተጨማሪ ጎል ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። ረጃጅም ኳሶችን አዘውትረው የታዩት ድሬዳዋ ከተማዎች ፈጣኖቹን ከወገብ በላይ የሚገኙ ተጫዋቾቻቸው እንቅስዋሴ ላይ የተመረኮዘ ጥቃት መሰንዘራቸውን ይዘዋል። በዚህ አጨዋወትም 24ኛው ደቂቃ ላይ ናንጄቦ ከርቀት የተላከለትን ኳስ በመጠቀም ወደ ጎል የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭታ መዳረሻዋ የአቤል እቅፎች ውስጥ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ኳሱን በትዕግስት በመቀባበል የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል ለመጎብኘት ሲጥሩ ተስተውሏል። በ37ኛው ደቂቃም ዊሊያን እና አቡበከር በድጋሜ የተቀናጁበትን ኳስ አቡበከር ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ፍሬው ጌታሁን አጋጣሚውን አምክኖታል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩትም የተገኘን የቅጣት ምት ፍሬው በአግባቡ ማውጣት ሳይችል ቀርቶ የተመለሰውን ኳስ አማኑኤል ከአቡበከር ተቀብሎ ወደ ግብ ቢመታውም የግቡ አግዳሚ ዕድሉን አክሽፎታል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በፈጣን እንቅስቃሴዎች ታጅቦ የተጀመረው ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል አስቆጪ እድሎችን ይዞ ብቅ ያለ ነበር። አጋማሹ በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃም አቡበከር ከሚኪያስ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ፍሬው በጥሩ ቅልጥፍና ሲያድንበት በ54ኛው ደቂቃ ደግሞ ናንጄቦ ከረጅም ርቀት የተላከለትን ኳስ ግብጠባቂው አቤልን አልፌ አገባለሁ ብሎ ለማለፍ ሲጥር አቤል በጥሩ አቋቋም እና ጊዜ ኳሱን ተረክቦታል።

በጨዋታው ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በ58ኛው ደቂቃ በድጋሜ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃም የድሬዳዋ ተከላካዮች በሚገባ ማውጣት ያልቻሉትን ኳስ አስራት ቱንጆ አግኝቶት ግብ አስቆጥሯል። ቡድኑ መሪ ከሆነ በኋላም በተሻለ መዝናኖት ጨዋታውን ሲከውን ታይቷል። 75ኛው ደቂቃ ላይም የቡድኑን የመጀመሪያ ጎል ያስቆጠረው አቡበከር በግል ጥረቱ እየገፋ ሄዶ ወደ ጎል በመታው ኳስ መሪነቱን ሊያሰፋ ነበር። ይህ የአቡበከር ጥረት መና ቢቀርም አቤልን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው እንዳለ ደባልቄ የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት አሳድጓል። በ84ኛው ደቂቃም ተጫዋቹ ከአላዛር ሽመልስ የደረሰውን ጥሩ ኳስ ከመረብ አሳርፏል። በሁለተኛው አጋማሽ ይባስ ተዳክመው የታዩት ድሬዳዋዎች የኢትዮጵያ ቡናን ጥቃት መመከት ተስኗቸው እጅ ሰጥተው ወጥተዋል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በሰበሰቧቸው 13 ነጥቦች አስረኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ሲቀመጡ ጨዋታውን በድል የደመደሙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ነጥባቸውን ሠላሳ በማድረስ ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር ያላቸውን ልዩነት በስምንት አስቀጥለዋል።





© ሶከር ኢትዮጵያ