ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አርባምንጭ ከተማ ድሬዳዋን ከተማን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አስራ ስድስተኛ ሳምንት ሁለተኛ መርሐግብር አርባምንጭ ከተማ በመሠረት ወርቅነት ብቸኛ ጎል ድሬዳዋ ከተማን 1ለ0 መርታት ችሏል፡፡

ከጅምሩ ለአርባምንጭ ከተማዎች ምቹ በነበረው ጨዋታ ኳስን በማደራጀት በተለይ በመስመር በኩል በፍጥነት ኳሶችን ወደ አጥቂ ክፍል በማሻገር ጥቃት ሰንዝረዋል። ቀስ በቀስ ግን ወደ ጨዋታ ቅኝት የገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በሒደት የተሻሉ ሆነዋል፡፡

በታደለች አብርሀም አማካኝነት ወደ ግብ መድረስ የቻለው የምስራቁ ክለብ አስቆጪ ሙከራን 38ኛው ደቂቃ ላይ አድርጓል፡፡ ቁምነገር ካሣ በፈጣን ሽግግር ከፀጋነሽ ወራና ያገኘችውን ኳስ ከግቡ ትይዩ ቦታ ላይ እንዳገኘች በቅፅበት ወደ ግብ ብትመታም የግቡ ቋሚ ብረት መልሶባታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ብዙአየው ጀምበሩ አጥቂዎቿ ይታይባቸው የነበረውን ክፍተት የተመለከተች በሚመስል መልኩ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾችን አከታትላ ቀይራ ወደ ሜዳ አስገብታለች፡፡ ሆኖም በፍላጎት ሲጫወቱ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች በ51ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል፡፡ ፅዮን ሳህሌ ወደ ግራ አዘንብላ ወደነበረችው ታታሪዋ መሠረት ወርቅነት በረጅሙ የላከችላትን ኳስ የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮችን ስህተት በሚገባ ያስተዋለችው አጥቂዋ ሁለት ጊዜ ኳሱን ገፋ ካደረገች በኃላ ከመረብ አሳርፋ ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ በፈጣን አጥቂዎቻቸው እገዛ ተሻጋሪ ኳሷች ላይ ድሬዳዋዎች ማድረግ ቢችሉም የአርባምንጭ ተከላካዮችን አልፎ አቻ ለመሆን ግን አልቻሉም፡፡ እታለም አመኑ ከቅጣት ምት መታ ግብ ጠባቂዋ ድንቡሽ አባ ስትይዝባት እንዲሁን ከማዕዘን የተሻማን ኳስ ሀሳቤ በግንባር ገጭታ ብታስቆጥረውም የዕለቱ ዋና ዳኛ አዳነች ታደሰ ጎሉ ከመቆጠሩ በፊት ጥፋት ተፈፅሟል በማለት ግቧን ሽራታለች፡፡

ለሁለት ደቂቃዎች ያህል ድሬዳዋዎች በግቧ መሻር ቅሬታን ቢያሰሙም በሁለተኛ ቅጣት ምት ጨዋታው ቀጥሎ በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት አርባምንጭ ከተማዎች 1ለ0 አሸናፊ ሆነው ወጥተዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ