አዳማ ከተማ አራት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ግርጌ ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች አራት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን በዛሬው ዕለት አስፈርመዋል።

በአሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እያሳዩ ያሉት አቋም የወረደ ነው። ይህንን ተከትሎም ክለቡ በውድድር ዓመቱ የሠበሰባቸውን ነጥቦች ሁለት አሀዝ ማድረስ ሳይችል በደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። አሠልጣኙም ክለቡን ከተረከቡ በኋላ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ በማምጣት ከአስጊው ቀጠና ለማስወጣት እየሞከሩ ይገኛሉ። በዛሬው ዕለትም አራት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾቸን ወደ ስብስባቸው መቀላቀላቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

የመጀመሪያው ተጫዋች ማማዱ ኩሊባሊ ነው። ማሊያዊው አጥቂ ባሳለፍነው ወር በተጠናቀቀው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ እስከ ፍጻሜው መጓዝ የቻለ ሲሆን በግማሽ ፍፃሜው ማሊ ጊኒን በመለያ ምቶች አሸንፋ ስታልፍ የመጨረሻውን የፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ነበር፡፡ ኩሊባሊ ከዚህ ቀደም ኤምሲ አልጀርስ፣ አል ሂላል፣ ዱባይ ካልቸራል ስፖርትስ ክለብ፣ ፉስ ራባትና ስታዴ ማሊያን ተጫውቶ ማሳለፉ ታወቃል፡፡

ሁለተኛው ተጫዋች ላሚኔ ኮማሬ ነው። ማሊያዊው የመሐል ተከላካይ ተጫዋች ወደ አዳማ ከመመወጣቱ በፊት ኤ ኤስ ፖሊስ ለሚባል ክለብ ሲጫወት ነበር። ከኮማሬ በተጨማሪ 2012 ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለመቐለ 70 እንድርታ ሲጫወት የነበረው የመሐል ተከላካዩ ላውረንስም አዳማን ተቀላቅሏል። ግዙፉ ተከላካይ ከሲዳማ ቡና ጋር መለያየቱን ተከትሎም የቀድሞ አሰልጣኙን ተከትሎ መዳረሻው አዳማ ሆኗል።

አራተኛው ተጫዋች ደግሞ ኤሊሴ ዲማንኬል ነው። ቡርኪናፋሶዋዊው የአማካይ ተከላካይ ተጨዋች ከዚህ ቀደም አሴክ አቢጃን፣ ኤስፔራንስና ኤኤስኤፍ ያኔጋ መጫወት ችሎ ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ