“…እኛም አንሰማም” – እንዳለ ደባልቄ

ፈርጣማው አጥቂ እንዳለ ደባልቄ ዛሬ ጎል አስቆጥሮ ደስታውን ስለገለፀበት መንገድ ለሶከር ኢትዮጵያ ይናገራል። 

ኢትዮጵያ ቡና ከባለፉት ዓመታት የተሻለ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። በባህር ዳር ቆይታ የመጨረሻው ጨዋታም ድሬዎችን ሦስት ለአንድ በመርታት አጠናቋል። የጨዋታውን የማሳረጊያውን ሦስተኛ ጎል ተቀይሮ በመግባት ያስቆጠረው እንዳለ ደባልቄ ነው። እንዳለ ባሳለፍነው ዓመት በተሰረዘው የውድድር ዘመን ጥር ወር በዘጠነኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ጎል ካስቆጠረ በኃላ ከጎል ርቆ የቆየው አጥቂው ዛሬ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጎሉን አስቆጥሯል። ጎሉንም ካስቆጠረ በኃላም ጆሮውን በሁለት እጆቹ በመድፈን ደስታውን ስለገለፀበት ሁኔታ ለሶከር ኢትዮጵያ አጋርቷል።

” በእግርጥ ከዓምናው ዘንድሮ ብዙ የመሰለፍ ዕድሎችን እያገኘሁ አይደለም። ያው የአሰልጣኛችን ውሳኔ ነው። ሁሌም በሚሰጠኝ እድል ግን ለቡድኔ የምችለውን አደርጋለው።

” ጎል ካስቆጠርኩ ትንሽ ጊዜው ርቋል። ያው ዓምና ኮሮናም መጣ ውድድርም ተሰረዘ በዚህ ምክንያት ትንሽ ጊዜውን አስፍቶታል። ብቻ ከጎል መራቅ በጣም ከባድ ነው። የተሻለ ለመሥራት እየጣርኩ ባለሁበት ወቅት ዛሬ የዓመቱ የመጀመርያ ጎሌን በማስቆጠሬ ደስ ብሎኛል። በቀጣይም ቡድኑ የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ቻምፒዮን እንዲሆን ነው እየሰራን ነው። እኔም በተሰጠኝ ዕድል እና አጋጣሚ ጎል በማግባት ቡድኔንም እራሴንም ለመጥቀም አስባለሁ።

” ጎሉን አስቆጥሬ ጆሮዬን በእጄ በመድፈን ደስታ የገለፅኩበት ምክንያት… በዚህ ሰዓት ከፍተኛ የሆነ የዋንጫ ፉክክር ያለበት ሊግ ነው። መሪው ትንሽ ውጤቱን አስፍቶብን ነበር። የግዴታ በዛሬው ጨዋታ በማሸነፍ ውጤቱን ማጥበብ ስለነበረብን እኛም አንሰማም በማለት ለመሪው ቡድን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። እነርሱ ትናንት ጎል አስቆጥረው በዚህ መልኩ ደስታቸውን ገልፀው ስለነበረ የመልስ ምት ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ