ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የባህር ዳር ቆይታ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ባለፉት ቀናት ተከናውነዋል። በአስራ ስድስተኛው ሳምንት የተደረጉት ጨዋታዎች ላይ የታዩ ዐበይት ጉዳዮችንም እንደሚከተለው ቃኝተናል።
👉 ዐፄዎቹ የሚገዳደራቸው ጠፍቷል
በ16ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪው ፋሲል ከነማ ጅማ አባጅፋርን ገጥሞ በሙጂብ ቃሲም ሁለት ግቦች በመርታት መሪነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
ምንም እንኳን ከባባድ ተጋጣሚያቸውን በተከታታይ በመርታት ለዚህኛው ጨዋታ ቢደርሱም ጅማ አባ ጅፋር ውጤቱን አብዝቶ ከመፈለጉ አንፃር ሊፈትናቸው ይችላል ተብሎ የተጠበቁት ፋሲሎች ከጅምሩ የበላይነታቸውን አሳይተዋል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር እንዳደረጉት ሁሉ ከፍ ባለ ግለት የጀመሩትን ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በግዙፉ አጥቂያቸው ባስቆጠሯቸው ጎሎች ጨርሰው መውጣት ችለዋል። ዐፄዎቹ የዋንጫ ቡድን ባህሪያቸውን በደግሚ ባሳዩበት ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው ጋር ያላቸው ልዩነት የደረጃ ብቻ ሳይሆን የስብስብ ጥራት ፣ በራስ የመተማመን እና ጨዋታን በራስ መንገስ የማስኬድ ብቃትም ጭምር እንደሆነ ማሳየት ጀምረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በላይኛውም ሆነ በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል ካለ ቡድን ጋር ሲገናኝ ተመሳሳይ ትኩረትን ተላብሶ ወደ ሜዳ እንደሚገባም አስመልክቷል።
ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብን ያሳኩት ዐፄዎቹ በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች በአራቱ አሸንፈው በአንዱ ብቻ አቻ የተለያዩ ሲሆን ሊጉ ለቀናት ከመቋረጡ በፊት በ38 ነጥብ እየመሩ ይገኛል። ከአምስት ሳምንታት በኋላ በሀዋሳ እና በሰበታ ጨዋታ የተቆጠሩባቸውን ጎሎች ወደ ጎን ትተውም ለሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ግብ ሳያስተናግዱ መውጣት ሲችሉ ከሽንፈት ጋር ከተለያዩም 13 ጨዋታዎች አልፈዋል።
👉 ኢትዮጵያ ቡና ፋሲልን መከተሉን ቀጥሏል
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሊጉ መሪ ሽንፈትን አስተናግደው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 3-1 በመርታት ከመሪው ፋሲል ከተማ ጋር ያላቸውን የስምንት ነጥብ ልዩነትን አስጠብቀው መቀጠል ችለዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ያሸነፋቸው ፋሲል ከነማን ውጤት አይተው ወደ ሜዳ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የነጥብ ልዩነቱ መስፋት ጫና ውስጥ እንደሚከታቸው ይጠበቅ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በጉዳት ያጣቸው ተጫዋቾች እንደመኖራቸውም መነቃቃት ላይ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ ከባድ ፈተናን እንደሚሰጠው ታስቧል። ነገር ግን ገና ከጅምሩ በአቡበከር ናስር ፈጣን ግብ መምራት ያቻሉት ቡናዎች ጁኒያስ ናንጄቦ በፍጥነት አፀፋውን ቢመልስባቸውም ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እና እንደሁል ጊዜውም የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ ጨዋታውን ያለብዙ ጭንቀት ድል ማድረግ ችለዋል። ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ሽንፈት የመለሳቸውን የፋሲልን ውጤት በቶሎ ወደ ኋላ ትተው ዳግም ወደ አሸናፊነት መመለሳቸው በድሬዳዋው ውድድር የዋንጫ ፉክክራቸውን ባልተቀዛቀዘ ስሜት ለመቀጠል እጅግ ወሳኝ እንደሚሆንላቸውም መናገር ይቻላል።
በሊጉ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመሪው ፋሲል ከተማ በስምንት ነጥብ ቢርቁም አሁንም በሰላሳ ነጥብ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ይገኛሉ። ከተከታያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስም የአራት ነጥቦች ልዩነት መፍጠራቸው በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ በሚያደርገው ቦታ ላይ የመቆየት ዕድላቸውን ያሰፋዋል።
👉 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፉክክሩ እየራቀ ይገኛል
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ዋነኛ ተገዳዳሪ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ ቀስ በቀስ ከፉክክሩ እየራቁ ያለ ይመስላል። በዚህ ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየው ቡድኑ ከመሪው ፋሲል በ12 እንዲሁም ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና በ4 ነጥቦች ርቆ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በስብስብ ደረጃ በርካታ በሊጉ ደረጃ ጥራታቸው የላቀ ተጫዋቾችን ያሰባሰበው የቅዱስ ጊዮርጊስ በወጥነት የሚጠበቅበትን ውጤት ለማስመዝገብ እየተቸገረ ይገኛል። ቡድኑ ውድድሩ በአዲስ ቅርፅ ፕሪሚየር ሊግ በሚል ስያሜ ከ1990 ጀምሮ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለሦስተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን ዋንጫ ያለማንሳቱ ነገርም እርግጥ እየሆነ የመጣ ይመስላል።
ቀሪ ጨዋታዎች ቢቀሩም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪዎቹ ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እንኳን በቅድሚያ የራሱን የቤት ሥራ የሆነውን ጨዋታዎችን ማሸነፍ በቅጡ ለመከወን እየተቸገረ ነው። ከበላዩ ያሉት ቡድኖች ወቅታዊ ግስጋሴ አንፃር ሲታይም ቀስ በቀስ ከፉክክሩ እየራቀ መሆኑ ግልፅ ይመስላል። ከመጨረሻው የወልቂጤ ድሉ በኋላ በሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦች ማሳካቱ ብቻ ሳይሆን የሊጉን ክብር የማግኘት ተስፋ ያለው ቡድንን የማይመጥን የሜዳ ላይ ብቃት እያሳየ መሆኑ ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክር ነጥብ ነው።
👉 የጣናው ሞገድ ባህር ዳርን በድል ተሰናብቷል
የወጥነት ጥያቄ የሚነሳበት ባህርዳር ከተማ በውደድር ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ባስመዘገበበት የአዳማ ከተማው ጨዋታ በፍፁም ዓለሙ ብቸኛ ግብ የከተማውን ቆይታ በድል ደምድሟል።
በዘጠና ደቂቃዎች ከተጋጣሚያቸው አንፃር ፍፁም የበላይነት የነበራቸው ባህርዳሮች ኳስን በትዕግሥት በመቆጣጠር ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሙከራ አድርገዋል። የተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ሆነ እንጂ በርከት ያሉ ግቦችን ማስቆጠር በቻሉ ነበር። ይህን ነጥብ ከተጋጣሚያቸው ደካማነት ጋር ማስተሳሰር ቢቻልም የጣና ሞገዶቹ በትክክል መነቃቃት ማሳየታቸውን ግን መካድ አይቻልም። በትኩረት ማጣት ይታማ የነበረው ቡድኑ በመቀመጫ ከተማው ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ እንዲሁም ያለሽንፈት አስር ነጥቦችን ማሳካቱ ለዚህ በቂ ማስረጃ እንደሆነ መናገር ይቻላል። በመጀመሪያ ጨዋታ ነጥብ የጣሉት ባህር ዳር ከተማዎች በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ መስብሰብ ችለዋል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ አራተኝነት ከፍ ማለት የቻሉት ባህር ዳሮች በጅማ ቆይታቸው የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች የጣሏቸው ነጥቦች ከምንም በላይ አሁን ላይ የሚያስቆጫቸው ይመስላል።
👉 ነብሮቹ ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኋላ አሸንፈዋል
ከሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በኃላ ነብሮቹ እየተንገዳገደ የሚገኘው ሲዳማ ቡናን 2-0 በመርታት ከዋንጫ ፉክክሩ ሙሉ ለሙሉ ላለመራቅ ያላቸውን ተስፋ ያለመለሙበትን ድል አስመዝግበዋል።
የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉት ሀዲያ ሆስዕናዎች የሊጉን ዋንጫ የማሸነፍ ምኞት ብቻ ሳይሆን ዕቅዱም ያላቸው ይመስል ነበር። ነገር ግን ከአዲስ አበባው ውድድር በኋላ ቡድኑ እንደቀድመው ጊዜ ተደጋጋሚ ድሎችን ማሳካት እየተሳነው በውጤት ዝርዝሩ ውስጥ አቻ እየበረከተ መጥቷል። አልፎ አልፎ በጠባብ ውጤት ከሚያሸንፍባቸው ጨዋታዎች ውጪም ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ላለመንሸራተት ጠንካራው የመከላከል አደረጃጀቱ ብቃት ላይ ለመመርኮዝ ተገዶ ቆይቷል። ይሁን እና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ይህ ጠንካራ ጎኑም ከድቶት ተከታታይ ሽንፈቶችን ማስተናገዱ ከዋንጫ ፉክክሩ እንዲርቅ፤ ወደ ታች መንሸራተት እንዲጀምርም አድርጎት ነበር።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከሲዳማ ቡና በተገናኘበት ጨዋታ ጅማሮ ላይም ብልጫ ተወስዶበት ቢታይም እንደ ሁል ጊዜው በሩን በአግባቡ በመከርቸም ብቃቱ ታግዞ መሪነቱን በማስጠበቅ የ2-0 ድልን ማጣጣም ችሏል። ቡድኑ አሁን ላይ የነጥብ ስብስቡን 26 አድርሶ ከተስተካካዮቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ በግብ ልዩነት ተበልጦ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዚህም የቻምፒዮንነት ህልሙ እንደመጀመሪያው እጁ ላይ ነው ባይባልም ከላይ ባለው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ግን አልተሳነውም።
👉 እዛው መርገጣቸውን የቀጡሉት ሲዳማ እና አዳማ
በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ የነበሩበት አጠቃላይ ሁኔታ በመጠኑ ልዩነት ያለው ቢሆንም ራሳቸውን ለማሻሻል የሄዱበት መንገድ ግን ተመሳሳይነት አለው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን ሁለቱም ከሽንፈት የዘለለ የመጣላቸው መልካም ነገር የለም።
ከጅምሩም በደካማ ስብስብ ወደ ውድድሩ የመጣው አዳማ ከተማ ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበረው ጅማ አባ ጅፋርን ማሸነፍ ይቻል እንጂ ቀጣይ መንገዱ ቀላል እንደማይሆንለት ግልፅ ነበር። ያለፉት ዓመታት ድንቅ ስብስቡን በፋይናንስ ድክመቱ ከማጣቱ ባሻገር በጥቂቱም ቢሆን ተመሳሳይ ቡድን ለመገንባት አለመቻሉ ለአስከፊ የውድድር ዓመት ዳርጎታል። ከዚህ በተለየ ወሳኝ ተጫዋቹን አዲስ ግደይን ከማጣቱ በቀር የተለየ የስብስብ መፋለስ ያልገጠመው ሲዳማ ቡናም እንደወትሮው የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሲጠበቅ ከአደጋ ዞን በጥቁቱ ከፍ ብሎ ከመቆየት የዘለለ ውጤት ለማምጣት ተቸግሯል። ነባር የቡድኑ ተጫዋቾች አቋም ከሌላው ጊዜ ወርዶ መታየቱ በቶሎ አለመስተካከሉም ስጋቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ አባብሶበታል።
በዚህ ሁኔታ ወደ ውድድሩ አጋማሽ የደረሱት ሁለቱ ክለቦች የመጡበትን መንገድ በመገምገም ተመሳሳይ አካሄድን መርጠዋል። ሁለቱም አዳዲስ አሰልጣኞችን መቅጠራቸው እንዲሁም ከቀሪዎቹ የሊጉ ክለቦች በተለየ በተጫዋቾች ዝውውር መጠመዳቸው ተስፋን የሚያጭር ሆኖላቸውም ነበር። ስር ነቀል ሊባል የሚችል ለውጣቸው የእስካሁኑ ውጤት ግን ያሰቡትን ያሳካ አይመስልም።
የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው ሲዳማ ቡና አራት ጨዋታዎችን አድርጎ አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር ያለምንም ነጥብ ባህር ዳርን ተሰናብቷል። ከውጤት ባሻገር የዕውር ድምብር የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም ወደ ውጤት ለመመለስ ብዙ ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችል የሚያሳይ ሆኗል። ለሲዳማው ዘርዓይ ሙሉን ነፍስ የመዝራት ተልዕኮ የሰጠው አዳማም በእንቅስቃሴ ረገድ መጠነኛ ተስፋ ከማጫር ያለፍ ነገር ሳይታይበት ሦስተኛ ሽንፈቱን ለመቀበል ተገዷል።
ለሀገራችን የክለብ አስተዳደር ድክመት ምሳሌ መሆን የሚችሉት ሁለቱ ክለቦች ምስጋና ከበላያቸው ላሉት ቡድኖች ድክመት ይገባና ተስፋቸው አሁንም እንዳለ ቢሆንም ያፈሰሱት ሀብት ጊዜውን የጠበቀ አለመሆን ትዝብት ውስጥ የሚጥል ነው። ድሬዳዋ ላይ በሚቀጥለው ውድድር እርስ በእርስ ሲገናኙስ ማን ተሽሎ ይታይ ይሆን የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ