ሁለት ተጫዋቾች ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ ሲሆኑ በምትኩ አንድ ተጫዋች ተጠርቷል

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቱን ትናንት የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት አማካዮችን በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሲያደርግ በምትኩ አንድ ጫዋች መጥራቱ ታውቋል።

በባህር ዳር ብሉ ናይል ሆቴል ተቀምጦ ዝግጅት ማድረግ የጀመሩት ዋልያዎቹ በስብስባቸው 25 ተጫዋቾች አካተው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከነዚህ መካከል አማካዮቹ አማኑኤል ዮሐንስ እና አብዱልከሪም ወርቁ በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል። ሁለቱ ተጫዋቾች በክለባቸው ቆይታቸው ከገጠማቸው ጉዳት በማገባ እንዳላገገሙ የተነገረ ሲሆን በአስሬ ስድስተኛው ሳምንት ጨዋታዎች የወልቂጤ ከተማው አብዱልከሪም ተቀይሮ መውጣቱ፣ የኢትዮጵየ ቡናው አምበል ደግሞ በመጀመርያው አጋማሽ ተቀይሮ መግባቱ የሚታወስ ነው።

የሁለቱን ተጫዋቾች ከስብስቡ ውጪ መሆን ተከትሎ የፋሲል ከነማው አማካይ ይሁን እንደሻው ጥሪ ደርሶታል። ብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው የመጀመርያ ሁለት የማጣርያ ጨዋታዎች ላይ ግልጋሎት ሰጥቶ የነበረው አማካዩ ዛሬ አመሻሽ ወደ ባህር ዳር አምርቶ ስብስቡን እንደሚቀላቀል ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ