በዚህ ሳምንት የተደረጉትን ጨዋታዎች ተመርኩዘን ተጫዋች ነክ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።
👉 የተጫዋቾች ጉዳት የተደራረበበት ኢትዮጵያ ቡና
ከመሪው ፋሲል ከነማ በ8 ነጥብ ርቀው በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት እየተቸገሩ ይገኛሉ።
የመስመር አጥቂያቸው ሀብታሙ ታደሰን ከሳምንታት ጉዳት መልስ ከማግኘታቸው ውጪ ሌሎች የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ጉዳት እየጎበኛቸው ይገኛል። የመስመር ተከላካዩ ኃይሌ ገብረተንሳይ በአዳማ ከተማው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን ታፈሰ ሰለሞን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት እንዲሁም ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን በድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ በጉዳት ከሜዳ ወጥተዋል።
ለተመሳሳይነት የቀረበ የመጀመሪያ 11 ተመራጭ ተጫዋችን የሚጠቀመው ቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ጉዳት ማስተናገዳቸው ስጋት የሚፈጥር ሲሆን ሊጉ በቀጣይ ለሦስት ሳምንታት የመቋረጡ ነገር ለኢትዮጵያ ቡና በጥሩ ጊዜ የመጣ የእፎይታ ጊዜ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
👉 ስንታየሁ መንግሥቱ ከአስደናቂ ግብ ጋር ተመልሷል
የውድድር ዘመኑ ሲጀመር የወላይታ ድቻን የፊት መስመር እንዲመራ ከፍተኛ ዕምነት ተጥሎበት የመጣው የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ቁመተ መለሎ አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱ በመጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን በማስቆጠር መልካም አጀማመር ማድረግ ችሎ ነበር።
ነገር ግን ቡድኑ በአምስተኛ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥም ጉዳት ካስተናገደ ወዲህ ላለፉት ስምንት የጨዋታ ሳምንታት በጉዳት ምክንያት ቡድኑን ማገልገል ሳይችል ቀርቷል። ለሁለት ጨዋታዎች ተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጥ የቻለው አጥቂው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን ሲገጥም ከሁለት ወራት በኋላ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ወደ ሜዳ ዳግም ተመልሶ ለቡድኑ ጨዋታ ማድረግ ችሏል።
ወደ ሜዳ በተመለሰበት በዚሁ የመጀመሪያ ጨዋታውም በ10ኛው ደቂቃ ቡድኑን መሪ ያደረገችን ግብ ከሳጥን ጠርዝ በግሩም አጨራረስ ምስቆጠር ችሏል። የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ዕምነት አግኝቶ ከጉዳት በተመለሰበት ጨዋታ ለ60 ደቂቃዎች ያህል በሜዳ ከመቆየቱ ባለፈ ኳስ እና መረብን በማገናኘቱም ለቀጣይ ጨዋታዎች ከፍ ባለ በራስ መተማመን እንዲመለስ እንደሚረዳው ይጠበቃል።
👉 አህመድ ሁሴን አሁንም አስቆጥሯል
በ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ግቡን ለማግኘት እስከ 15ኛ የጨዋታ ሳምንት ለመጠበቅ ተገዶ የነበረው የወልቂጤ ከተማው አጥቂ አህመድ ሁሴን ሁለተኛዋን ግብ ለማግኘት ግን ጥቂት ቀናት ብቻ ነበር ያስፈለጉት።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ወልቂጤ ከተማዎች ጅማ አባጅፋርን ሲረቱ የመጀመሪያ ግቡን ያስቆጠረው ተጫዋቹ ከወላይታ ድቻ ጋር 1-1 በተለያዩበት ጨዋታ ደግሞ በቄንጠኛ አጨራረስ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ችሏል። አጥቂዎች ከግብ ጋር ተኳርፈው ሲቆዩ በራሳቸው ላይ ያላቸው ዕምነት መሸርሸሩ አይቀርም። ሆኖም በቶሎ በግብ ላይ ግብ መጨመር በፍጥነት ወደ አስፈላጊነታቸው ይመልሳቸዋል። የአህመድ ሁሴን በተከታታይ ማግባትም ለተጫዋቹ ብቻ ሳይሆን በቦታው የተፈጠረበትን ክፍተት መድፈን ከብዶት ለነበረው ወልቂጤ ከተማም ተስፋ የሚሆን ይመስላል።
👉 የእንዳለ ደባልቄ ጎል እና የደስታ አገላለፁ
ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን በረታበት ጨዋታ አቤል ከበደን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ እንዳለ ደባልቄ በ84ኛው ደቂቃ የቡድኑን ማሳረጊያ ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል።
በተሰረዘው የውድድር ዘመን ጥር ወር ላይ በዘጠነኛ ሳምንት መርሐግብር ቡድኑ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሲዳማ ቡናን ሲረታ በፍፁም ቅጣት ምት ጎል ካስቆጠረ በኋላ ባሁኑ ሳምንት የውድድር ዓመቱ የመጀመርያውያ ጎሉን ያስቆጠረው ተጫዋቹ ግቧን ካስቆጠረ በኋላ ጆሮውን በሁለት እጆቹ በመድፈን ደስታውን ሲገልፅ አስተውለናል።
ስለ ሁኔታውም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረገው እንዳለ ይህን ብሏል።
” ከፍተኛ የሆነ የዋንጫ ፉክክር ያለበት ሊግ ነው። መሪው ትንሽ ውጤቱን አስፍቶብን ነበር። የግዴታ በዛሬው ጨዋታ በማሸነፍ ውጤቱን ማጥበብ ስለነበረብን እኛም አንሰማም በማለት ለመሪው ቡድን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ጎሉን አስቆጥሬ ጆሮዬን በእጄ በመድፈን ደስታ የገለፅኩት። እነርሱ ትናንት አግብተው በዚህ መልኩ ደስታቸውን ገልፀው ስለነበረ የመልስ ምት ነው።”
👉 የፍፁም ዓለሙ አስደናቂ ጎል
የባህርዳር ከተማ እስተንፋስ እንደሆነ እያስመሰከረ የሚገኘው አማካዩ ፍፁም ዓለሙ በዚህ ሳምንት ቡድኑ የባህርዳር ቆይታውን በድል እንዲደመድም ያስቻለች ወሳኝ ግብን አስቆጥሯል።
በ22ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ ፍፁም ዓለሙ ተቀብሎ የአዳማን ተጫዋቾች ከቀነሰ በኋላ ከአዳማዎች የሳጥን ጠርዝ ላይ በኃይል ሳይሆን ክህሎት በተሞላበት አስደናቂ አጨራረስ እጅግ ማራኪ የሆነችን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
እንደ ዐምናው ሁሉ በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው የአጥቂ አማካዩ በአስፈላጊው ሰዓት በሳጥን ውስጥ የሚገኝበት ብቃቱ በርካታ ጎሎች እንዲያስቆጥር የረዳው ሲሆን የጎሉን ቁጥር ስምንት በማድረስ ከሊጉ አማካዮች ከፍተኛውን የጎል ቁጥር አስመዝግቧል።
👉 የኮከቦቹ መመለስ
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ ስማቸው በልዩነት ከሚጠሩ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል ናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢ እና ዑመድ ኡኩሪ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ለአዳዲስ ቡድኖቻቸው የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገዋል።
የቀድሞው የመከላከያ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ መሰመር ተጫዋቾች የሆነው ኡመድ ኡኩሪ በግንቦት 2006 ጀምሮ ላለፉት ሰባት ዓመታት በግብፅ ሊግ በሚገኙት ኢቲሀድ አሌክሳንድሪያ ፣ ኤንፒ ፣ ኤል ኢንታግ ኤል ሀርቢ ፣ ሰሞሃ ፣ አስዋን የተጫወተው አጥቂ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ከቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሰውን ዝውውር ማድረጉ ይታወሳል።
ሀዲያ ሆሳዕናን የተቀላቀለው ተጫዋቹ ቡድኑ ሲዳማ ቡና 2-0 በረታበት ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረግ ሲችል በጨዋታውም በ8ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ በጥሩ መልኩ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረብም መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።
በተመሳሳይ በ2010 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ቻምፒዮን በነበረው የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው ጅማ አባ ጅፋር ቡድን ውስጥ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ኦኪኪ አፎላቢም ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚመልሰውን ዝውውር ከፈፀመ ወዲህ ለአዲሱ ክለቡ ሲዳማ ቡና በሀዲያ ሆሳዕና በተረታበት ጨዋታ ላይ የመጀመሪያውን ጨዋታ አድርጓል።
ጨራሽ አጥቂን በእጅጉ ይፈልጉ ለነበሩት ሁለቱ ቡድኖች በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ፊርማቸውን ያኖሩት ሁለቱ ተጫዋቾች የቡድናቸውን ጥያቄ በምን መልኩ ይመልሳሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
👉 የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች እና ጉዳት
የዚህ ሳምንት ጨዋታዎችን መጠናቀቅ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያከናውናል። ለነዚህ ወሳኝ ጨዋታዎች በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከተጠሩ ተጫዋቾች መካከል የወልቂጤዎቹ ረመዳን ናስር እና አብዱልከሪም ወርቁ ቡድኑ ከወላይታ ድቻ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ጉዳት አስተናግደው ተቀይረው ወጥተዋል። በተለይም በዋልያዎቹ የግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ ቦታውን ያስከበረው ረመዳን በትከሻው ላይ በገጠመው ጉዳት ገና አጋማሹ ሳይጠናቀቅ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዶ ነበር። ሆኖም ሁለቱም ተጫዋቾች የገጠማቸው ጉዳት ከባድ እንዳልሆነ እና ለብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ከመስጠት እንደማያግዳቸው ታውቋል።
የወልቂጤ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ እንደመሆኑ የሁለቱ ተጫዋቾች ጉዳት በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ሌሎችተመረጡ ተጫዋቾች ሁኔታ ትኩረት እንዲስብ ያደረገ ነበር። እንደ ሱሌይማን ሀሚድ እና አስቻለው ታመነ ያሉ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው የተመለከቱ በርካቶችም ብሔራዊ ቡድኑ በጉዳት ሊመናመን ይሆን የሚል ስጋት እንዲያጭሩ አድርጓቸው ታይቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ