ሊግ ካምፓኒው ሰኞ ስብሰባ ይቀመጣል

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን በበላይነት እያስተዳደረ የሚገኘው ሊግ ካምፓኒው የፊታችን ሰኞ በቀጣይ በምታስተናግደው ድሬዳዋ ከተማ ዝግጅት ዙርያ ስብሰባ ያደርጋል።

እስካሁን ባለው የውድድር አፈፃፀም መልካም ተግባራቶች እየከወነ የሚገኘው የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የበላይ አስተዳዳሪ የሆነው የሊግ ካምፓኒው አዲስ አበባ ከተማ የጀመረው ውድድሩ ጅማ እና ባህር ዳር ላይ በተሳካ ሁኔታ ቀጥሎ አስራ ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። ቀጣይ ተረኛ የሆነችው ምስራቃዊቷ ከተማ ድሬዳዋ እንደሆነችም ይታወቃል።

ድሬዳዋ ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስችላት አቅም በምን ሁኔታ እንደሚገኝ ለመገምገም የሊግ ካምፓኒው በሁለት ዙር ወደ ስፍራው ተጉዞ መገምገሙ ይታወቃል። በመጀመርያው ዙር ግምገማ መስተካከል አለባቸው በሚሉ ጉዳዮች ዙርያ ከሳምንታት በፊት ምክረ ሀሳብ ሰጥቶ ቡድኑ መመለሱ ሲታወስ ከቀናት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረቧቸው ምክረ ሀሳቦች በምን ደረጃ ተሻሽሏል የሚለውን ለመታዘብ የልዑክ ቡድኑ የሦስት ቀናት ጉብኝት በማድረግ ረቡዕ አዲስ አበባ ገብቷል። በመጀመርያው ዙር አብዛኛው መስተካከል አለባቸው በማለት ያቀረበው ሀሳብ በሁለተኛው ዙር የመስክ ምልከታው ወቅት በሚገባ ተሻሽሎ እና ብዙ ለውጦችን ተደርገው እንደሚገኙ መታዘቡን እና በቀሩት 20 ቀናት ጥቂት የቀሩ ሥራዎች በትኩረት እንዲሰሩ አቅጣጫ ሰጥተው ተመልሰዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከተማዋ ውድድሩን በድምቀት ለማዘጋጅት የሚያስችላትን ሁኔታ ከሆቴል አቅርቦት፣ ከትራንስፖርት አሰጣጥ እና ከፀጥታ አንፃር ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን የመጫወቻ ሜዳንም ሆነ የልምምድ ሜዳዎችን በቂ ዝግጅት መደረጉን እንዲሁም ድሬደዋ ካለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን በመነሳት ጨዋታዎችን በምሸት ለማድረግ የመብራት ፓውዛ ተከላ መጠናቀቁን ሰምተናል። በድሬዳዋ በዚህ መልኩ ውድድሩን በጥሩ ሁኔታ ለማዘጋጀት ትንቀሳቀስ እንጂ በክለቦች በኩል ከልምምድ ሜዳ እጥረት አኳያ የሚነሱ ጥያቄዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።

በአጠቃላይ የድሬዳዋን የዝግጅት ሁኔታ በሁለት ዙር ሲገመገም የቆየው ሊግ ካምፓኒው ሰኞ በሚያደርገው ስብሰባ በቀጣይ በቅድመ ዝግጅቱ ዝርዝር ጉዳዮች ዙርያ የመጨረሻ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ