በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር በሁለት ምድብ ተከፍሎ አስራ ሦስት ቡድኖችን የሚካፈሉበት ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
ረፋድ ሦስት ሰዓት ጎፋ ሜዳ ላይ መከላከያን ከ ሀሌታ ያገናኘው ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ሳቢ ያልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ብዙም የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሳያስመለክተን ቢቀጥልም የተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ሀሌታዎች በመስመር አጥቂያቸው ሚካኤል ንጉሱ አማካኝነት የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጎል አስቆጥረዋል። ከዕረፍት መልስ ሀሌታዎች ተዳክመው ሲታዩ በአንፃሩ መከላከያዎች ተጭነው በመጫወታቸው የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት አንበሉ በኃይሉ ንጉሴ ወደ ጎልነት ቀይሮት ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በማስከተል በዚሁ ጎፋ ሜዳ በተካሄደው የአምስት ሰዓት ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በቡናማዎቹ ፍፁም የበላይነት አራት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሲሆኑ የቡናዎቹ ግብጠባቂ እና ተከላካይ ሲገባበዙ የሰሩትን ስህተት ተከትሎ አብዱልከሪም ማሙሽ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥረዋል።
አቡበከር ናስርን በታዳጊነቱ በማሰልጠን የሚታወቀው እና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና ታዳጊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን እየሰራ በሚገኘው አሰልጣኝ ደግፌ የሚመሩት ታዳጊዎቹ ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኃላ የበለጠ ተነቃቅተው በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በእንቅስቃሴ ብልጫ ወስደው በግሩም ሁኔታ የተደራጀውን ኳስ ዮሴፍ ብርሀኑ ወደ ጎልነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ትኩረት ሰጥተው ለውድድሩ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን እንቅስቃሴያቸው የሚገልፀው ኢትዮጵያ ቡናዎች በዮሐንስ ሙራድ ሁለተኛ ጎል ለዕረፍት ወጥተዋል።
ከእረፍት በኋላም ብልጫ መውሰዳቸውን የቀጠሉት ቡናዎች በያብስራ ተስፋዬ ድንቅ ሁለት ጎሎች ጨዋታውን አራት ለአንድ ማሸነፍ ችለዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት በኢትዮጵያው ቡናው ግብጠባቂ ኪሩቤል ገብረኢየሱስ መክኖባቸዋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል በእርጋታ እና ጨዋታ በማንበብ መሐል ሜዳ ላይ ኳስ የማደራጀት አቅሙን ሲያስመለክተን የዋለው አንበሉ ሱራፌል ሰይፈ የወደፊቱ ተስፈኛ ተጫዋች እንደሚሆን ከወዲሁ መናገር ይቻላል።
በጃን ሜዳ ጠዋት አራት ሰዓት በጀመረው ሌላ ጨዋታ ቤተል ድሪምስ ከ ከላላ ያደረጉት ጨዋታ በከለላ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል። ለቤተል ድሪምስ በኩል ካሊድ መሐመድ ጎል ቢያስቆጥርም የኃላ የኋላ ከለላዎች በዮሴፍ በቀለ ሁለት ጎሎች አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። ለከለላ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ቡድኑን አሸናፊ ያደረገው ዮሴፍ በቀለ ጎሉን ካስቆጠረ በኃላ ወደ ተቃራኒ ቡድን በመሄድ ፀያፍ የሆነ ስድብ እና ምልክት በማሳየት በፈፀመው ያልተገባ ድርጊት ምክንያት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
ቀትር ስድስት ሰዓት የቀጠለው የፍቅር በአንድነት እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ በአዳማ ሦስት ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጠንካራ ቡድን ይዘው የቀረቡት የውድድሩ ተጋባዥ አዳማዎች ዮሴፍ ታረቀኝ እና ሳዲቅ ዳሪ በክፍት እንቅስቃሴ ጎል ሲያስቆጥሩ ሦስተኛውን የማሳረጊያ ጎል አቡበከር ሀባስ በቅጣት ምት ጎል ጨዋታውን ሦስት ለዜሮ አሸንፈዋል።
ስምንት ሰዓት በተካሄደው ሌላ መርሐ ግብር ጌታቸው ቀጨኔ በዲኤፍቲ ለደርዘን የተጠጋ ጎል ተስተናግዶበት አስር ለዜሮ ተሸንፎ ወጥቷል። እንደወሰዱት ብልጫ ሁሉ በርከት ያሉ ጎሎችን ያስቆጠሩት ዲኤፍቲዎች በሄኖክ ኤምያስ ሐት ትሪክ ጎሎች ሲያገኙ ተቀይሮ በመግባት ሁለት ጎሎችን አቤል ሚካኤል ሲያስቆጥር ሌሎቹን ሁለት ጎሎች ዳዊት ሽፈራው አስቆጥሮ የዲኤፍቲዎችን የጎል መጠን ወደ ሰባት ከፍ አድርገውታል። የቀሩትን ሦስት ጎሎች እዮብ ብርሀኑ አልሀሚድ ሙሀጅር እና አብዱልፈታ ኑረዲን አስቆጠረው አስር ለምንም አሸንፈው ወጥተዋል።
በዲኤፍቲ በኩል የቦታ አየያዙ፣ ተጫዋቾች በሚገርም ክህሎት የሚቀንስበት መንገድ እና ጎል በማስቆጠር የአጨራረስ ብቃቱን ያስመለከተን እንዲሁም የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሐት ትሪክ የሰራው ሄኖክ ኤርምያስ ወደ ፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደሆነ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
የመጀመርያው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የኢትዮጵያ መድን እና የአፍሮ ፅዮን ጨዋታ በአፍሮ ፅዮን ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል። የኢትዮጵያ መድን ብቸኛ ጎል ሳላዲን አብደላ ሲያስቆጥር ለአፍሮ ፅዮን ይታገሱ ታሪኩ እና ቅዱስ ዮሴፍ አስቆጥረዋል። የአፍሮ ፅዮኑ ቅዱስ ዮሴፍ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ድንቅ አጥቂ እና የወቅቱ የኢትዮጵያ ቡና የተስፋ ቡድን አሰልጣኝ የሆነው ዮሴፍ ተስፋዬ ልጅ ነው።
ሣራ ካኒዛሮ የዚህ ምድብ አራፊ ቡድን ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ውድድር ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ቢቆይም ከኮቪድ ፕሮቶኮል ስጋት የተነሳ ራሱን ከውድድሩ አግልሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ