ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አቃቂ ቃሊቲ የዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን በአዳማ ላይ አሳካ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአስራ ስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አቃቂ ቃሊቲ አዳማ ከተማን 1ለ0 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ሦስት ነጥብ ጨብጧል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ የእንቅስቃሴ የበላይነት በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን በቅብብል ከፈጣሪ አማካዮቹ ኪፊያ አብዱራህማን እና ዙለይካ ጁሀድ በሚገኙ አደገኛ ኳሶች በአዳማ ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ገና ከጊዜ ነበር፡፡ 3ኛው ደቂቃ ላይም ልዩነት ፈጣሪ የነበረችው ኪፊያ ወደ ግራ መስመር ተሰላፊዋ ዮርዳኖስ በርሄ አሾልካ ሰጥታ በሳጥን ውስጥ ኳሱን ያገኘችው የመስመር ተጫዋቿ በፍጥነት ሞክራ ለጥቂት በወጣባት አጋጣሚ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡

በጨዋታ እንቅስቃሴ ኳስን በማንሸራሸሩ አቃቂዎች በተሻለ የሜዳ ላይ ቆይታ የነበራቸው ሲሆን አዳማ ከተማዎች የግብ ዕድልን ለመፍጠር የተጠቀሙበት የጨዋታ መንገድ በግራ መስመር ወደተሰለፈችው የምስራች ላቀው ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ አጨዋወታቸውን በመስመር ያድርጉ እንጂ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተጠቀሙበት በቆሙ ኳሶች ነው፡፡ 20ኛው ደቂቃ በቀኝ የአቃቂ የግብ ክልል የተገኘን ቅጣት ምት የምስራች ላቀው ወደ ጎል መታ በግቡ አናት የወጣባት የክለቡ የመጀመሪያ ሙከራ ሆኗል፡፡ 25ኛ ደቂቃ አልፊያ ጃርሶ ከቅጣት ምት ወደ ጎል አክርራ የመታቻት ኳስ የግቡን ቋሚ ብረት ነክታ የተመለሰችባት ሌላዋ ቡድኑ ያገኘው ጥሩ አጋጣሚ ቢሆንም ወደ ጎል ለመለወጥ የነበራቸው ተነሳሽነት የተቀዛቀዘ ሆኖ ታይቷል፡፡

ከሰላሳ ደቂቃዎች በኃላ ኳስን በቁጥጥራቸው ስር ያዋሉት አቃቂዎች በተሻለ ፈጣን እንቅስቃሴ ተደጋጋሚ ዕድልን ፈጥረዋል፡፡ በዙለይካ ጁሀድ ዳግም ወደ ግብ ክልል የደረሱት አቃቂዎች በቤዛዊት፣ ዮርዳኖስ፣ ኪፊያ እና ዙለይካ አስደናቂ ጥምረት ታግዘው የጠሩ አጋጣሚዎችን ለማግኘት ጥረዋል፡፡ ቤዛዊት ንጉሴ ከትዕግስት ዘውዴ ጋር በቅብብል ሳጥኑ ጠርዝ ስትደርስ ወደ ጎል መታው ግብ ጠባቂዋ ፎዚያ አድናባታለች፡፡

ከእረፍት መልስ በሙከራ ረገድ ከመጀመርያው የተቀዜቀዘ ሲሆን 73ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን ግብ አስመልክቶናል። ከቀኝ የአዳማ የግብ ክልል ወደ ማዕዘን ምት ከተጠጋ ቦታ ላይ አቃቂዎች ያገኙትን የቅጣት ምት አምበሏ አስናቀች ትቤሶ አሻምታ ተከላካይዋ ፌቨን መርከብ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር አቃቂን መሪ አድርጋለች፡፡

አዳማ ከተማዎች መደበኛው ዘጠና ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠ ጭማሪ ሰዓት ላይ ከጥሩ ቦታ ላይ የቅጣት ምት ቢያገኙም አልፊያ ጃርሶ መታው በቀላሉ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ይዛባት ጨዋታው 1ለ0 በአቃቂ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ከሳምንት በፊት አሰልጣኝ ብዙዓየው ዋዳን ያሰናበተው ክለቡ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብን ይዟል፡፡ በሊጉ ለመቆየት በሌሎች ውጤት ላይ የተመሰረተ ጠባብ ዕድል ይዞ ቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎችን የሚያደርግም ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ