ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ16ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በባህር ዳር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በመመስረት ሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ስብስብ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ አካታለች።

አሰላለፍ (4-1-4-1)


ግብ ጠባቂ

ባሕሩ ነጋሽ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች የተሻሉ ሆነው የታዩ ግብ ጠባቂዎች ተቀራራቢ አቋም ያሳዩ ሲሆን ከመሀላቸው ባሕሩ ነጋሽን ትመራጭ አድርገነዋል። ለሁለተኛ ተከታታይ ሳምንት በስብስባችን የተካተተው ባህሩ በጥሩ እርጋታ እና የጊዜ አጠባበቅ ጨዋታውን ያከናወነ ሲሆን በተለየም የብሩክ በየነን ድንቅ የሳጥን ውጪ ሙከራ ያመከነበት መንገድ በመምራት ላይ የነበረው ጊዮርጊስ በቶሎ አቻ እንዳይሆን አድርጎ ነበር።

ተከላካዮች

እንየው ካሣሁን – ፋሲል ከነማ

ከአዲስ አበባው የመጨረሻ ጨዋታ የሰዒድ ሀሰን ጉዳት ጀምሮ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው እንየው በመልካም አቋሙ እንደቀጠለ ነው። በዚህም ሳምንት ከፍተኛ የማጥቃት ፍላጎቱ የቡድኑን የቀኝ ወገን ማጥቃት ተፅዕኖ ከፍ ያደረገው ሲሆን ሁለተኛው የሙጂብ ጎል እንዲቆጠር ምክንያት የነበረውን ተሻጋሪ ኳስ ትክክለኛውን ጊዜ በመጠበቅ ለአጥቂው ማድረስ ችሏል።

ሰለሞን ወዴሳ – ባህር ዳር ከተማ

ባሳለፈው ሳምንት እንድንመርጠው ያደረገውን ብቃት የደገመው ሰለሞን በተከታታይ የመሀል ተከላካያችን መሆን ችሏል። የተለምዶው ንቃቱ አብሮት በነበረበት ጨዋታ አልፎ አልፎ ይታይ የነበረውን አዳማ ከተማን ማጥቃት በሙሉ ትኩረት ሲያቋርጥ እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የበላይ ይሆን የነበረው ተጫዋቹ ከኋላ ጥቃት በማስጀመር ብቃቱም አንድ ያለቀለት የግብ ዕድል መፍጠር ችሎ ነበር።

ላውረንስ ላርቴ – ሀዋሳ ከተማ

ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ለሦስተኛ ጊዜ የምርጥ ቡድናችን አካል ሆኗል። ቅዱስ ጊዮርጊስን በገጠሙበት ጨዋታ አደገኛ ኳሶችን በማፅዳት ፣ በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ አጥቂዎችን በመቆጣጠር እና አልፎ አልፎ ረዘም ያሉ ኳሶችን በመላክ ጥቃት እያስጀመረ በጨዋታው ጥሩ ተፅዕኖውን ማሳየት ችሏል።

አሥራት ቱንጆ – ኢትዮጵያ ቡና

የብሔራዊ ቡድን ተመራጩ የግራ መስመር ተከላካይ እንደወትሮው ሁሉ በድሬዳዋው ጨዋታም የማጥቃት ድፍረቱን ደጋግሞ አሳይቷል። በዚህ ጥረቱም የቡድኑ ቀዳሚ ጎል እንዲቆጠር ምክንያት የሆነውን ጥቃት ሲያስጀምር ወደ ተጋጣሚው ሳጥን ዘልቆ መግባት በቻለበት አጋጣሚም የቡድኑን ሁለተኛ ግብ የአጥቂ በሚመስል አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

አማካዮች

ይሁን እንዳሻው – ፋሲል ከነማ

ከመጀመሪያ አሰላለፍ ርቆ የሰነበተው ይሁን የሀብታሙ ተከስትተን ቅጣት ተከትሎ ወደ ቀዳሚ አሰላለፍ በመጣበት ጨዋታ በሳምንቱ ከታዩ ተከላካይ አማካዮች የተሻለ
ብቃትን ማሳየት ችሏል። ወደ ብሔራዊ ቡድን ምርጫ መመለስም የቻለው አማካዩ በአዳማው ጨዋታ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ እንዲሁም ለአጥቂ አማካዮቹ ቀረቦ ቅብብሎችን በመከውን ባደረገው መልካም እንቅስቃሴ ኃላፊነቱን በጥሩ መወጣት ችሏል።

ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ

ታታሪው የመስመር ተጫዋች ለሦስተኛ ጊዜ በሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ መካተት ችሏል። በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ እንደሁል ጊዜው ሁሉ የቡድኑ የቀኝ ክፍል በማጥቃት ሂደት ውስጥ የነበረው አበርክቶት ከፍተኛ ለመሆኑ ምክንያት የነበረ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሙጂብ ቃሲም የመጀመሪያ ጎል እንዲቆጠር ምክንያት የነበረውን ኳስ ማቀበልም ችሏል።

ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ

ከአራት ሳምንታት በኋላ ወደ ምርጥ ቡድናችን የተመለሰው አስፈሪው አማካይ ከአዳማ ጋር ልዩ ሆኖ ታይቷል። ቡድኑን አሸናፊ ያደረገችውን ብቸኛ ግብ እጅን በአፍ በሚያስጭን መልኩ ከማስቆጠሩ ባለፈ ለምንይሉ ወንድሙ ያለቀለት የግብ ዕድል መፍጠር ሲችል የግል ብቃቱ ከተንፀባረቀበት ሌላ አጋጣሚም ኢላማውን የጠበቀ ከባድ ሙከራ አድርጎ መክኖበታል።

ወንድምአገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ

እስካሁን አንድ ጊዜ በተጠባባቂነት የያዝነው ወጣቱ አማካይ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጥ ቡድናችን ቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ መካተት ችሏል። በተለምዶው ትጋቱ የሀዋሳን የመሀል ክፍል ከዕድሜው በላይ በሆነ ብስለት የመራው ተጫዋቹ ከእስከዛሬው በታሻለ ለግብ ቀርቦ የተንቀሳቀሰ ሲሆን ቡድኑ አቻ የሆነበት ግብ ሲቆጠርም ሦስት የጊዮርጊስ ተከላካዮችን በሰውነት እንቅስቃሴ ጥሎ ዋናውን ሥራ መስራት ችሏል።

ዊሊያም ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና

ወጣቱ አማካይ ልዩ ብቃቱን ካሳየባቸው ጨዋታዎች የዚህ ሳምንቱ የድሬዳዋው ጨዋታ ቀዳሚው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የቴክኒክ ብቃቱ እና እይታው ለተጋጣሚዎቹ ፈተና ሆኖ በታየበት በዚህ ሳምንት ለአቡበከር ናስር ሁለት ያለቀላቸው ዕድሎች መፍጠር ችሎ አንዱ ወደ ግብ ሲቀየር ለሦስተኛው ግብ መገኘት መነሻ የነበረውን ተንጠልጣይ ኳስ ወደ ሳጥን በማድረስም የበኩሉን አድርጓል።

አጥቂ

ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ግብ ወደማስቆጠሩ የተመለሰው ሙጂብ ይበልጥ ተነቃቅቶ የታየበትን ሌላ 90 ደቂቃ ያስመለከተን በመሆኑ በምርጫችን ተካቷል። ቡድኑ ፋሲል ጅማ አባ ጅፋርን ሲገጥም አምስት ኳሶችን ወደ ግብ የሞከረው ግዙፉ አጥቂ ሁለቱን ከመረብ በማሳረፍ የጨዋታውን ውጤት በጊዜ መወሰን ችሏል።


አሰልጣኝ – ካሣዬ አራጌ

የኢትዮጵያ ቡናው አለቃ ለሦስተኛ ጊዜ የድረገፃችን የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ ሆነው ተመርጠዋል። ከሽንፈት የተመለሰውን እና በመጀመሪያ ተሰላፊዎቹ ላይ ጉዳቶች ያስተናገደውን ቡድን አዋቅረው ጥሩ መነቃቃት ላይ በመሆኑ ሊፈትናቸው ይችላል ተብሎ የነበረው ድሬዳዋ ከተማን ያለብዙ ችግር ማሸነፍ ችለዋል።

ተጠባባቂዎች

አቡበከር ኑሪ – ጅማ አባ ጅፋር
ተስፋዬ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
ይበልጣል ሽባባው – ወልቂጤ ከተማ
ሬድዋን ናስር – ኢትዮጵያ ቡና
ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ
ኤፍሬም አሻሞ – ሀዋሳ ከተማ
አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና


© ሶከር ኢትዮጵያ