የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ተራዘሙ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ዲቪዚዮን የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት የሚደረጉበት ቀናት ተራዝመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ዲቪዚዮን የ2013 ውድድር የአንደኛው ዙር መርሃግብር በሀዋሳ ተደርጎ ከተጠናቀቀ በኃላ የሁለተኛው ዙር ከየካቲት 6 ጀምሮ በአዳማ ከተማ እየተደረገ ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎችን ብቻ ይጠብቃል፡፡ ቀደም ብሎ በወጣው መርሐግብር መሠረት ውድድሩ መጋቢት 11 እንደሚጠናቀቅ የተገለፀ ቢሆንም በሦስት የተለያዩ ምክንያቶች ከክለቦች ጋር በተደረገ ውይይት መራዘሙን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የውድድር ሰብሳቢው አቶ ጌታቸው የማነብርሀን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሰብሳቢው ገለፃ ከሆነ አርባምንጭ ከተማዎች በገጠማቸው የመኪና አደጋ ከኤሌክትሪክ የነበረባቸው ተስተካካይ ጨዋታ መጋቢት 13 ስለሚደረግ የመራዘሙ አንደኛው ምክንያት ሲሆን የሁለተኛ ዲቪዚዮን መጋቢት 12 ስለሚጠናቀቅ ከአንደኛ ዲቪዚዮኑ ጋር የፕሮግራም መጋጨት እክል እንዳይፈጥር እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማዳጋስካር ጋር በዚህ ወር አጋማሽ ጨዋታ ስላለበት በመዝጊያው ዕለት መኖር የነበረባቸው እንግዶች ላይኖሩ ስለሚችሉ እነሱንም ታሳቢ በማድረግ የፍፃሜውን ቀን መጋቢት 19 እንዲሆን ተወስኗል።

ከሴተች ፕሪምየር ሊግ ጋር በተያያዘ በሁለቱም የዲቪዚዮን ውድድሮች ላይ በኮከብ ተጫዋችነት. ግብ አስቆጣሪነት እና በምርጥ አሰልጣኝነት እንዲሁም በምስጉን ዳኝነት ለሚያጠናቅቁ እንደተለመደው በአንድ ሆቴል በሚደረግ ሥነ ስርዓት ሽልማታቸው እንደሚበረከት ለማወቅ ችለናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ