የዋልያዎቹ ጨዋታ የቴሌቪዥን ሽፋን ያገኝ ይሆን?

በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚደረገው የኢትዮጰያ እና ማዳጋስካር ጨዋታ በቴሌሊዥን የሚተላለፍበት ዕድል እንዳለ እየተጠቆመ ይገኛል።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2022 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎቹን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጋቢት 15 ወሳኝ ጨዋታውን ከማዳጋስካር ጋር ያከናውናል።

ስድስት ነጥቦችን ይዞ የምድቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑም ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ ጨዋታው በሚደረግበት ባህር ዳር ልምምዱን እያደረገ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መጋቢት 15 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚደረገውን የምድቡ አምስተኛ ጨዋታንም ሱፐር ስፖርት በቀጥታ ለማስተላለፍ ቅድመ ዝግጅቱን እያደረገ እንደሆነ ሰምተናል።

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን ከባህር ዳር ከተማ ለ21 ቀናት በቀጥታ ሲያስተላልፍ የነበረው የሱፐር ስፖርት የቀጥታ ስርጭት ጊዜያዊ ስቱዲዮም (መኪና) በአሁኑ ሰዓት እዛው በባህር ዳር እንደሚገኝ ሶከር ኢትዮጵያ ያረጋገጠ ሲሆን የብሔራዊ ቡድኑን ጨዋታን ካስተላለፈ በኋላ ወደ ድሬዳዋ እንደሚጓዝ ተነግሯል። ጨዋታውን የሚያስተላልፉ የቴክኒክ እና ካሜራ ባለሙያዎችን ጨምሮ የተቋሙ ጋዜጠኞችም የፊታችን ሰኞ ወደ ስፍራው ለመጓዝ ቀጠሮ እንደያዙ ሰምተናል።

በተያያዘ ዜና የአማራ ቴሌቪዥንም ከሱፐር ስፖርት ጋር በመጣመር ለስፖርት ቤተሰቡ ጨዋታውን በሌላ አማራጭነት ሊያስተላልፍ የሚችልበት ዕድልም እንዳለ ተነግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ