​ዋልያዎቹ የወዳጅነት ጨዋታቸውን በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል

በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም የማላዊ አቻውን በወዳጅነት ጨዋታ የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 4-0 ማሸነፍ ችሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታውን ተክለማርያም ሻንቆን በግብ ጠባቂነት አሥራት ቱንጆ ፣ ያሬድ ባየህ ፣ አስቻለው ታመነ እና ረመዳን የሱፍን በተከላካይ ስፍራ በማሰለፍ ነበር የጀመረው። ቡድኑ መሀል ላይ መስዑድ መሐመድ ፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ሽመልስ በቀለን ሲጠቀም ሽመክት ጉግሳ ፣ ጌታነህ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ደግሞ የፊት መስመሩን ሸፍነዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ፈጠን ባለ ማጥቃት ነበር የጀመረው። ገና በሁለተኛው ደቂቃ አብዝቶ በማጥቃት ላይ ይሳተፍ የነበረው ረመዳን የሱፍ ባሻገረው ኳስ የመጨረሻ የግብ ዕድል ፈጥረው የነበረ ሲሆን በመቀጠል ጌታነህ ከበደ ያደረገው የሳጥን ውስጥ ሙከራም ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ መሆን የቻሉት ዋልያዎቹ ተጋጣሚያቸው በራሱ ሜዳ እንዲቀር ማድረግ የቻሉ ሲሆን 16ኛው ደቂቃ ላይ ብልጫቸውን በግብ ማጀብ ችለዋል። ሽመልስ በቀለ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ከጎሉ ፊት ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው መስዑድ መሀመድ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል።

በአመዛኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ቅብብል ለማቋረጥ ጥረት በማድረግ ያሳለፉት ማላዊዎች አልፎ አልፎ ወደ ፊት ለመሄድ የጣሩ ሲሆን የመጀመሪያውን የግብ ዕድል የፈጠሩት ግን 32ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከቆመ ኳስ መነሻውን ባደረገ ኳስ በግንባር ያደረጉት ሙከራም ወደ ውጪ የወጣ ነበር። በዋልያዎቹ የጨዋታ ብልጫ በቀጠለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በተጋጣሚያቸው ሳጥን ውስጥ ያለመናበብ እየታየባቸው ቢቆዩም ዋልያዎቹ ከዕረፍት በፊት መሪነታቸውን ማስፋታቸው አልቀረም። 45ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግራ ካደላው የመስዑድ መሀመድ ቅጣት ምት የተነሳውን ኳስ ረመዳን የሱፍ በግንባሩ አሳልፎለት ጌታነህ ከበደ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ይሁን እንዳሻው ፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፣  አቡበከር ናስር እና ሙጂብ ቃሲምን በሀብታሙ ተከስተ ፣ መስዑድ መሀመድ ፣ ሽመክት ጉግሳ እና ጌታነህ ከበደ ቦታ ተክተዋል።

በጨዋታው መሐል ከቀናት በፊት በአሳዛኝ ሁኔታ በደረገሰበት ጥቃት ህይወቱ ያለፈው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ቴዎድሮስ አበባየሁ በህሊና ፀሎት ታውሷል።

አጋማሹ ሲጀመር ማላዊዎች ዋልያዎቹን ከሜዳቸው እንዳይወጡ ማድረግ ችለዋል። ከሚነጥቋቸው ኳሶች ወደ ግብ በደረሱባቸው አጋጣሚዎችም በሮቢን ንግላንዴ ሁለት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች አድርገው ነበር። ነገር ግን ቀስ በቀስ ቅብብሎቻቸው የሜዳውን አጋማሽ ማለፍ እንዲችሉ በማድረጉ የተሳካላቸው ኢትዮጵያዊያኑ በድጋሚ ግብ ቀንቷቸዋል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ከአቡበከር ናስር የተመቻቸለትን ኳስ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት  ድንቅ ግን አስቆጥሯል። ማላዊዎች በቶሎ ምላሽ ለመስጠት ሞክረው ቮንሰንት ኖያንጉሉ ከተካልካዮች ጀርባ አምልጦ በመግባት ያረገውን ሙከራ ተክለማርያም አድኖበታል።

በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ሙጂብ ቃሲም ተጨማሪ ሙከራዎችን ያደረጉት ዋልያዎቹ በቀጣይ ደቂቃዎች ፍፁም ዓለሙ እና ጋዲሳ መብራቴን በሽመልስ በቀለ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ምትክ ወደ ሜዳ አስገብተዋል። የጨዋታ ብልጫቸው በነበረበት ቢቀጥልም ማላዊዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከባድ አጋጣሚ ፈጥረው ሹማክር ኩዋሊ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ግን ሱራፌል ከይሁን የደረሰውን ኳስ ሰንጥቆለት አቡበከር በተለመደ ፍጥነቱ ከተከላካዮች መሀል አምልጦ በመግባት አራተኛ ግብ አስቆጥሯል።

77ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ከቀማው ኳስ ያለቀለት ዕድል ፈጥሮ ሙጂብ እና አቡበከር በተከታታይ ሳይጠቀሙበት ከቀሩ በኋላ ጨዋታው ዛሬ የቀብር ሥነ -ስርዓቱ የተፈፀመው የኢትዮጵያ ቡናው ደጋፊ ቴዎድሮስ አበባውን ለማሰብ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጎበታል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ማላዊዎች በመልሶ ማጥቃት ግብ አፋፍ ለመድረስ ጥረት እያደረጉ ከመጨረሻ ደቂቃው የጆን ባንዳ የርቀት ሙከራ ውጪ የሰመረ ዕድል መፍጠር ተስኗቸው ሲቆዩ ዋልያዎቹም የጨዋታ ብልጫቸውን አሳልፈው ባይሰጡም አስፈሪ ሙከራዎችን ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጋቢት 15 ላይ በዛው የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከማዳጋስካር  ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚጫወት ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ