ማዳጋስካር ያለ ወሳኝ ተጫዋቾቿ ኢትዮጵያን ልትገጥም ነው

ከዋልያዎቹ ጋር ወሳኝ የምድብ የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ የሚጠብቃቸው ማዳጋስካሮች በጨዋታው ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን እንደማያገኙ ተሰምቷል።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የአህጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። በምድብ 11 ከማዳጋስካር፣ ኒጀር እና ኮትዲቯር ጋር የተደለደሉት ዋልያዎቹም የምድቡ ወሳኝ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን ለመከወን እየተሰናዱ ይገኛሉ። የፊታችን ረቡዕ’ም በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ማዳጋስካርን ያስተናግዳሉ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአውሮፓ ሀገራት እንደ አዲስ እየተንሰራፋ እንደሆነ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም በትናንትናው ዕለት በፈረንሳይ አንደኛው እና ሁለተኛው የሊግ እርከኖች ላይ የሚገኙ ክለቦች ስብሰባ አድርገው ስለ ኮቪድ እና ቀጣዩ የብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ውይይት አድርገዋል። ኤል ኤፍ ፒ (LFP) ባደረገው ስብሰባም በሊጉ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከአውሮፓ ኅብረት እና ከአውሮፓ ኢኮኖሚክ ቀጠና ውጪ ወደሚገኝ ሀገር እንዳይወጡ ክልከላ አስተላልፈዋል። ይህንን ተከትሎም በፈረንሳይ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚጫወቱ ወደ 150 የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ለሀገራቸው የሚሰጡት ግልጋሎት አይኖርም። ከዚህ መነሻነትም የፊታችን ረቡዕ ባህር ዳር በመምጣት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የምትገጥመው ማዳጋስካር ወሳኞቹን የቡድን ተጫዋቾች ሞሬል፣ ሞምብሪስ፣ ራያን እና ማቲያስን በጨዋታው እንደማታገኝ ተነግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ