ሴቶች ፕሪምየር ሊግ| ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቻምፒዮንነቱን አረጋገጠ

በአስራ ሰባተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ንግድ ባንክ ለረጅም ደቂቃ በአዳማ ከተማ ሲመራ ቆይቶ ተቀይራ በገባችው ፎዚያ መሐመድ ጎሎች በማሸነፍ አንድ ጨዋታ እየቀረው የ2013 የሊጉ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በመጀመሪያው አርባ አምስት አዳማ ከተማዎች በእንቅስቃሴም ይሁን ወደ ጎል በመሞከር ረገድ ብልጫን ያሳዩ ሲሆን ባንኮች አጀማመራቸው ጥሩ ያልነበረ ቢሆንም በሒደት ወደ እንቅስቃሴ በመግባት ሙከራኮች አድርገዋል።

ገና 3ኛው ደቂቃ ላይ ገነሜ ወርቁ ከምርቃት ፈለቀ ጋር በመጋጨቷ ጉልበቷ ላይ ጉዳት ደርሶባት በዓለምነሽ ገረመው ተቀይራ ወጥታለች።

እንቅስቃሴያቸው ከንግድ ባንክ ሻል ባለ መልኩ ሜዳ ላይ ሲያሳዩ የነበሩት አዳማዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት አልፊያ አክርራ መታ የግቡ ቋሚ ብረት በመለሰባት ቅፅበት የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በማድረጉ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች መረጋጋት ያልታየባቸው ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ቀዳሚ ሙከራቸውን ያደረጉት 14ኛው ደቂቃ ላይ ነበር፡፡ አረጋሽ ካልሳ ከግራ መስመር ከረሂማ የተቀበለችውን ኳስ ተጫዋቾችን አልፋ ከግብ ጠባቂዋ እምወድሽ ጋር ተገናኝታ አስቆጠረችው ተብሎ ሲጠበቅ ተከላካዮች ተረባርበው አስጠለዋታል፡፡

ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ በይበልጥ የማጥቂያ አማራጫቸውን ከመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ያደረጉት ንግድ ባንኮች በተወሰነ መልኩ ከጉዳት ከተመለሰችው ብርቱካን ገብረክርስቶስ እግር ከሚነሱ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል። ምንም እንኳን ተጫዋቿ አመቻችታ ያለቀላቸውን ኳሶች ስትሰጥ ቢስተዋልም ከፊት የነበሩት ሶስቱ አጥቂዎች ችኩልነት ስለነበረባቸው በቀላሉ ሲያመክኑት ታይቷል፡፡ ብርቱካን ሰጥታት አረጋሽ ወደ ሳጥን ገብታ ያመለጣት እና 35ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ብርቱካን ለሎዛ ሰጥታት ሎዛ ብትመታውም እምወድሽ ይርጋሸዋ የመለሰችባት የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

በረጃጅም ኳስ የባንክን የመከላከል ድክመት ለመጠቀም የጣሩት አዳማዎች በናርዶስ ጌትነት አማካኝነት በድጋሚ የጠራ አጋጣሚን ፈጥረዋል። ተሳክቶላቸውም መሪ ሆነዋል፡፡ መደበኛው የመጀመሪያ አርባ አምስት ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ ሲቀረው በመልሶ ማጥቃት ወደ ቀኝ መስመር የተሻገረላትን ምርቃት ፈለቀ በአግባቡ ተቆጣጥራ ሁለቴ ገፋ ካደረገች በኃላ በቀጥታ ስታሻማ ሰርካአዲስ ጉታ በግንባር በመግጨት አዳማን መሪ አድርጋለች።

በሁለተኛው አጋማስ ንግድ ባንኮች በተሻለ ተነሳሽነት የጨዋታ ብልጫን አሳይተዋል፡፡ ሰናይት ቦጋለ ባደረገችው ሙከራ ወደ ተጋጣሚ መጠጋት የጀመሩት ባንኮች የአዳማን ተከላካይ ክፍል ሲያልፉ ይታዩ እንጂ ግብ ጠባቂዋ እምወድሽ ይርጋሸዋ ግቧን በቀላሉ አላስደፈረችም። ለዚህም ማሳያ ብዙዓየው ታደሰ በቀኝ በኩል ወደ ሳጥን ይዛ ገብታ እምወድሽ የመለሰችባት እና 66ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ አንድ ለአንድ ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ የመለሰችባት ምናልባት ባንክን ወደ መሪነት የሚያሸጋግሩ የሆኑ ነበር፡፡

የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን ሌሎች አጋጣሚዎች ሲያገኙ የሚታዩ ቢሆንም አጥቂዎቹ ረሂማ እና ሎዛ ኳሱን ለማግኘት እርስ በእርስ የሚያደርጉት ያልተገቡ ያለመግባባቶች በተወሰነ መልኩ ቡድኑን ሲረብሽ በሜዳ ላይ መታየት ችሏል፡፡

ባንኮች 75ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳን ቀይራ የገባችው ፎዚያ መሐመድ ከገባች በኃላ ይበልጥ የማጥቃት ኃይላቸውን ጨምረዋል፡፡ 84ኛው ደቂቃ ላይም አቻ ሆነዋል፡፡ ሎዛ አበራ ከግራ የአዳማ የግብ አቅጣጫ ወደ ጎል ስታሻማ ወጣቷ አጥቂ ፎዚያ በሚገባ ተቆጣጥራ ተቀይራ በገባች በዘጠኝ ደቂቃ ውስጥ ጎል ከመረብ አገናኝታ ቡድኑን 1ለ1 አድርጋለች፡፡ የጨዋታው ሙሉ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠ የጭማሪ ደቂቃ ከመስመር ሲሻገር ተከላካዮች ጨራርፈው ያገኘችውን ኳስ የአካዳሚ ፍሬዋ ፎዚያ ለራሷ እና ለቡድኗ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ንግድ ባንክ እንዲያሸነፍ ረድታለች። ቡድኑም የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ከአምስት ዓመት በኋላ የተገኘውን ድል ተከትሎ የንግድ ባንክ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች በተለየ የደስታ ስሜት ሆነው ታይተዋል፡፡



© ሶከር ኢትዮጵያ