ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ከተማን ከመመራት ተነስቶ በመጨረሻዎቹ ስድስት ደቂቃዎች ባስቆጠሩት ጎል 2ለ1 በማሸነፍ አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው የሊጉ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ክለቡ አሸናፊነቱን እንዲያረጋግጥ ተቀይራ ገብታ ሁለት ግብ ያስቆጠረችው ተስፈኛዋ አጥቂ ፎዚያ መሐመድ ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ስሜቷን ለሶከር ኢትዮጵያ አጋርታለች፡፡ ትውልድ እና ዕድገቷ በምዕራብ ጎጃም ዞን ዱርቤቴ በምትባል አካባቢ ነው፡፡ በ2008 ክልሏ አማራን ወክላ በኮፓ ኮካ ኮላ ውድድር ላይ የተሳተፈችው ፎዚያ በውድድሩ ላይ ባሳየችው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተመልምላለች። በአካዳሚው ሦስት ዓመታትን ሰልጥና ካሳለፈች በኃላ 2011 ላይ በአሰልጣኝ የሺሃረግ ለገሰ ተመልምላ አዲስ አበባ ከተማን በመቀላቀል የክለብ ህይወቷን አንድ ብላ ልትጀምር ችላለች፡፡ በተሰረዘው የ2012 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መግባት የቻለችው ተስፈኛዋ ዐምና ጉዳት በማስተናገዷ ቡድኗን መጥቀም ባትችልም ዘንድሮ ግን ተቀይራ እየገባች ተስፈኝነቷን እያሳየች ትገኛለች፡፡ በዛሬው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዳማ ከተማ እስከ 84ኛው ደቂቃ ድረስ ሲመራ ቆይቶ 2ለ1 በማሸነፍ አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው ቻምፒዮን መሆኑን እንዲያረጋግጥ ያስቻሉ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለችው ፎዚያ “ተቀይሬ ገብቼ የቡድኑን ውጤት በመቀየሬ ደስ ብሎኛል። በተለይ ደግሞ ቻምፒዮን መሆናችን ከምንም በላይ ለእኔ የተለየ ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ ስንጠብቀው ነበር ይሄን ድል። በመሳካቱ በጣም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡” ስትል ለሶከር ኢትዮጵያ ከጨዋታው በኋላ አስተያየት ሰጥታለች። ዘንድሮ ተቀይራ በገባችባቸው ጨዋታዎች ጥሩ በመንቀሳቀስ አራት ጎሎች በስሟ ያስመዘገበችው ፎዚያ ተቀይራ ወደ ሜዳ ስትገባ በጥሩ ስሜት እንደሆነ ትገልፃለች። ” ወደ ሜዳ ስገባ አሰልጣኞች የነገሩኝ ትዕዛዝ ነበር። እናም ጎል እንደማስቆጥር ውስጤን አሳምኜ ነበር። በጣም ደስ የሚልም መንፈስን ይዤ ነበር ወደ ሜዳ የገባሁት። የምችለውን ነገር አድርጌ ወጥቻለሁ።” የቡድን ኅብረታቸው ለውጤታማነታቸው ዋና ምክንያት እንደሆነ የምትገልፀው አጥቂዋ የወደፊት እቅዷን በመግለፅ ከድረገፃችን ጋር የነበራትን አጭር ቆይታ ቋጭታለች። “ከእኔ የተሻሉ ትልልቅ ተጫዋቾች ጋር ነው የምጫወተው። ከእነሱ ልምድ በመውሰድ እነሱ ባሉበት ብሎም ከእነሱ ከፍ ባለ ደረጃ ደርሼ መጫወትን ነው የምፈልገው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ