የሉሲዎቹ ረዳት አሰልጣኞች ታውቀዋል

አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ለሀያ ስድስት ተጫዋቾች ትናንት ለወዳጅነት ጨዋታ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን መርጧል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቀጣዩ ወር መጀመሪያ ላይ ከደቡብ ሱዳን ጋር ለሚያካሂደው የወዳጅነት ጨዋታ የቡድኑ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ለሀያ ስድስት ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸውን በትናንትናው ዕለት መዘገባችን ይታወሳል፡፡ አሰልጣኙ ከስብሰባቸው በመቀጠል ደግሞ ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ የአሰልጣኝ መሠረት ማኒን ቦታ ተክታ ምክትል አሰልጣኝ መሆኗ የተረጋገጠ ሲሆን ቀደም ብሎ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሆኖ ቡድኑን ሲመራ የነበረው ሽመልስ ጥላሁን ደግሞ በዚሁ እንዲቀጥል ተወስኗል።

የአሰልጣኝነት ህይወቷን በዳሽን ቢራ ረዳት አሰልጣኝነት የጀመረችው ሰርካአዲስ በመቀጠል ዳሽን ቢራ እና እንዲሁም ጥረት ኮርፖሬትን በዋና አሰልጣኝነት በፕሪምየር ሊጉ ላይ መርታለች፡፡ዘንድሮ ባህር ዳር ከተማን እየመራች ሻምፒዮን በማድረግ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን እንዲያድግ ያስቻለችሁ እንስቷ ብሔራዊ ቡድኑን በረዳት አሰልጣኝነት ለቀጣዩ አንድ አመት ለማገልገል በብርሀኑ ግዛው ተመርጣለች፡፡

የቡድኑ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ተደርጎ በዛሬው ዕለት የተመረጠው ሽመልስ ጥላሁን (ፈሌ) ነው፡፡ ከዓመት በፊት በዚሁ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ቆይታ የነበረው የንፋስ ስልክ ላፍቶው አሰልጣኝ በኃላፊነት ቦታው እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ