የሊግ ካምፓኒው ልዑክ ድሬዳዋ ገብቷል

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በቀጣይ የምታስተናግደው ድሬዳዋ ከተማ በተለይ የምሽት ጨዋታን በማስተናገድ አቅሟ ዙርያ ግምገማ ለማድረግ የልዑክ ቡድኑ በስፍራው ተገኝቷል።

በተመረጡ የተመረጡ ከተሞች እየተካሄደ አስራ ስድስተኛ ሳምንት ላይ የደረሰው የዘንድሮው ቤትኪንግ ኢትዮጵያ የፕሪምየር ሊግ ውድድር ከአስራ አምስት ቀን በኋላ በቀጣይዋ ተረኛ አስተናጋጅ ድሬዳዋ አምስት የጨዋታ ሳምንታት የሚካሄድ ሲሆን ከተማዋም ለውድድሩ ማማር የተለያዩ ዝግጅቶች ስትከውን ቆይታለች። የመጫወቻ ሜዳውን ምቹ ለማድረግ ሥራዎች ተሰርተው የተጠናቀቁ እንደሆነ እየተገለፀ ሲገኝ ካለው የአየር ንብረት ሞቃታማነት አንፃር ጨዋታዎቹን እስካሁን ከተለመደው ሰዓት በተለየ ሁኔታ ምሽት ላይ ለማድረግ የከተማው ከአስተዳደር እና ናሽናል ሲሚንት ፋብሪካ በጋራ በመሆን የፓውዛ ተከላ እና የጄኔሬተር ግዢ ተፈፅሞ በአሁኑ ወቅት የሙከራ ሥራ እየተሥራ መሆኑ ተገልጿል።

ይህን የሙከራ ሁኔታ ለመከታተል እና የከተማዋ የምሽት ጨዋታዎችን የማድረግ ብቃቷን አይቶ ውሳኔ ለመስጠት እንዲያስችል ባሳለፍነው ማክሰኞ የሊግ ካምፓኒው ባደረገው ስብሰባ ወደ ስፍራው በማቅናት ሁኔታውን ማየት አስፈላጊ መሆኑን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉሥ የውድድር ክፍል ኃላፊ የሚመራ ልዑክ እና የዲኤስቲቪ ባለሙያዎች ዛሬ ድሬዳዋ በመግባት ምሽቱን ያለውን ሁኔታ እየገመገሙ ይገኛል።

በዚህም መሠረት በስፍራው የሚገኙ ባለሙያዎች ያለውን ሁኔታ ከተመለከቱ በኋላ በሚያቀርቡት ሪፖርት መነሻነት ጨዋታዎቹ የሚካሄዱበትን ሰዓት ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ