በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ለማድረግ እየተዘጋጀ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ በባህር ዳር እያደረገ ስለሚገኘው ዝግጅት ወቅታዊ መረጃዎችን እናጋራችሁ።
በሦስት ምዕራፍ የተከፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዝግጅት ጊዜ አሁን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ደርሶ በባህር ዳር እያደረገ የሚገኘው ዝግጅት ስምንተኛ ቀኑ ላይ ደርሷል። ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል አማኑኤል ዮሐንስ እና አብዱልከሪም ወርቁ በጉዳት ከብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጭ መሆናቸውን ተከትሎ አሰልጣኝ ውበቱ ይሁን እንደሻውን መተካታቸው ይታወቃል። ባሳለፍነው ረቡዕ ከማላዊ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በማድረግ አራት ለምንም ማሸነፉም ይታወሳል።
ከወዳጅነት ጨዋታው መልስ ብሔራዊ ቡድኑ ሐሙስ እና ዓርብ ቀለል ያለ ልምምድ የሰራ ሲሆን በዛሬው ዕለት ተጫዋቾቹ እረፍት እንዲያደርጉ ተደርጎ ከነገ ጀምሮ ወደ መደበኛ ልምምድ በመመለስ ለረቡዑ የማዳጋስካር ጨዋታ እየተዘጋጁ የሚቆዩ ይሆናል።
በማላዊ ጨዋታ ወቅት ከብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ ውጭ በመሆን ከቡድኑ ጋር ያልነበረው የባህር ዳር ከተማው ተከላካይ መናፍ ዐወል አሁንም ከቡድኑ ጋር ልምምድ እየሰራ አይገኝም። ከዚህ ውጭ ሁሉም የቡድኑ አባላት በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን መጋቢት 15 በባህር ዳር ከማዳጋስካር እና መጋቢት 21 አቢጃን ላይ ከአይቮሪኮስት ጋር ወሳኝ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ