አብዛኛው የጨዋታ ሳምንታቱ በወርሀ የካቲት ላይ ያረፈው የባህር ዳር ከተማውን የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቆይታ በመንተራስ በ30% የአንባቢያን እና በ70℅ የድረገፃችን ባልደረቦች ድምፅ ተከታዮቹን በወሩ ኮከብነት ሰይመናል።
የወሩ ምርጥ ተጫዋች – ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)
በጅማ ቆይታው ተዳክሞ የሰነበተው ባህር ዳር ከተማ ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማው ሲመጣ ዳግም ወደ ጥንካሬው ተመልሷል። ቡድኑ ያለሽንፈት ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች 10 ነጥቦችን ማሳካት ሲችልም የፍፁም ዓለሙ ጥንካሬ ጎልቶ መውጣቱ አልቀረም። በሁሉም ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ የቻለው ደፋሩ አማካይ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ካሳየው ብቃት በኋላ የተጋጣሚዎች ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ተፅዕኖው ቀንሶ የነበረ ቢሆንም በየካቲት ወር ግን አሁንም እጅግ አስፈላጊ ተጫዋች እንደሆነ ማሳየት ችሏል። ቡድኑ በ 16ኛው ሳምንት አዳማን ሲረታ ብቸኛውን ግብ በማራኪ ሁኔታ ከማስቆጠሩ ባለፈ ከኋላ ተነስቶ ማሸነፍ በቻለበት የሲዳማው ጨዋታም የአቻነቷን ግብ በስሙ ማስመዝገብ ችሏል። በዚህም በውድድሩ የከፍተኛ አግቢዎች ፉክክር ውስጥ እስከ 16ኛ ደረጃ ቢወርዱ ብቸኛው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ሆኖ የሚያገኙት ፍፁም የግብ ድምሩን 8 ማድረስ ችሏል።
ፍፁምን በግቦች ብቻ መግለፅ ግን ንፉግነት ይሆናል። በቡድኑ የማጥቃት መንገድ ከአጥቂው ጀርባ በነፃነት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና ያለው ተጫዋቹ የተጋጣሚዎች እሱን የማቆም ታክቲክ ዘወትር በታታሪነቱ በማፋለስ በየጨዋታው የማቀበያ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ ከማድረግ ባለፈ ራሱም የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር ታይቷል። አማካዩ በዚህ ዘርፍ ከአንባቢያን በተሰበሰበው ድምፅ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም በጥቅል ውጤት ግን በ79 ነጥቦች የወሩ ኮከብ መሆን ችሏል። የፋሲል ከነማው ያሬድ ባየህ በ68.5 ሁለተኛ ላዬ ሲቀመጥ የታኅሰየሣሥ እና ጥር ወር ኮከብ የነበረው የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ደግሞ በ55 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።
የወሩ ምርጥ አሰልጣኝ – ዘላለም ሺፈራው (ወላይታ ድቻ)
በጥቅሉ በዘንድሮው የውድድር ዓመት የወላይታ ድቻ ታሪክ የተቀየረው በአዲሱ አሰልጣኙ ሹመት ነው ቢባል ፈፅሞ ማጋነን አይሆንም። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በጅማው በቶሎ ወደ ውጤት የመለሱትን ቡድናቸውን ይዘው ወደ ባህር ዳር ቢያመሩም ቡድኑ በወራጅ ቀጠና ውስጥ
በመቆየቱ እና በአመዛኙ በወጣት ተጫዋቾች የተገነባ በመሆኑ ለውጡን ቀጣይነት ያለው ማድረግ በራሱ ከባድ ፈተና ነበር። በሥነ-ልቦናው ረገድ ጠንካራ እንዲሆን እና ከአደጋው ዞን ርቆ ያለስጋት እንዲቀመጥ ማስቻል ቀላል እንዳልሆነ ለመረዳት አሁን ላይ ከስር የሚገኙ ቡድኖችን ሁኔታ ማየት በቂ ነው።
ነገር ግን አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረጉት ከባድ ጨዋታ የጀመረውን ወር ያለምንም ሽንፈት ማገባደድ ሲችሉ የቡድኑን የመከላከል አቅም እጅግ በማሳደግ በአምስት ጨዋታዎች ከአንድ ጊዜ በላይ መረቡ እንዳይደፈር አድርገውታል። በውጤቱም ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ የመጣው ወላይታ ድቻ የወራጅ ቀጠናውን በአስር ነጥቦች ርቆ መቀመጥ ችሏል። በአንባቢዎቻችን ድምፅ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አሰልጣኝ ዘላለም ሺፈራው በድምር ውጤት ሌላው እጅግ ስኬታማ ወር ያሳለፉት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን በ6 ነጥቦች በልጠው 85 ነጥብ በመሰብሰብ የወሩ ምርጥ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ቡናው ካሣዬ አራጌ ደግሞ በ45 ነጥቦች ሦስተኛ ሆነዋል።
የወሩ ምርጥ ግብ ጠባቂ – ባህሩ ነጋሽ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
በግብ ጠባቂ ረገድ ተለዋዋጭ ምርጫ ከነበራቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቡድኑ ከሸገር ደርቢ በኋላ የፓትሪክ ማታሲን ቦታ ለለዓለም ብርሀኑ አስረክቦ ቢቆይም በተለይም በወልቂጤው ጨዋታ ላይ የነበረው የተጫዋቹ አቋም ወደ ሦስተኛው አማራጭ ፊቱን እንዲያዞር ያስገደደ ነበር። ከምርጫ ርቆ እና የጨዋታ ደቂቃዎች ማግኘት ተስንኖት ለቆየው ባህሩ ነጋሽ ይህ ቀላል ፈተና አልነበረም። በመጀመሪያ የተጋፈጠው የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ መሆኑ ደግሞ በወቅቱ ለጨዋታው ከተሰጠው ትልቅ ግምት አንፃር ፈተናውን የሚያጎላው ነበር። በዚህ ጨዋታ ላይ ጥሩ ብቃት ያሳየው ግብ ጠባቂው የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ያስተናግድ እንጂ ቀጣይ ዕድሎችን የሚያስገኝለትን ጊዜ ማሳለፍ ችሎ ነበር።
ባህሩ በቀጣይ በተደረጉት የድሬዳዋ ከተማ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፉ ሲቀጥል እጅግ አደገኛ የነበሩ ኳሶችን በማዳን ቅዱስ ጊዮርጊስ በደረጃ ሰንጠረዡ እንዳይንሸራተት በግሉ የሚጠበቅበትን ማድረግ ችሏል። ግብ ጠባቂው በ30% የአንባቢዎች ምርጫ አራተኛ ደረጃን ሲይዝ በድምር ውጤት 69.25 ነጥቦችን በመሰብሰብ የየካቲት ወር ኮከብ የግብ ዘብ ሆኗል። የወላይታ ድቻው መክብብ ደገፉ በ63 የፋሲል ከነማው ሚኬል ሳማኬ ደግሞ በ 51 ነጥቦች በተከታይነት ተቀምጠዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ