ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | በተስተካካይ ጨዋታ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን በ11ኛ ሳምንት መደረግ የነበረበት የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ዛሬ ተከናውኖ 1ለ1 ተጠናቋል፡፡

አርባምንጭ ከተማዎች የመኪና አደጋ አጋጥሟቸው ስለነበር ሳይደረግ በይደር የሰነበተው ጨዋታ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በቀኝ መስመር፤ አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው ሰናይት ባሩዳን ትኩረት ባደረገው የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴያቸው በይበልጥ ለመጠቀም አልመው የገቡበት እና በሜዳ ላይ ይህን አጨዋወት ልንመለከት የቻልንበት ነበረ፡፡ 7ኛው ደቂቃ ላይ ሣራ ነብሶ በዚሁ የጨዋታ መንገድ የመጣችን ኳስ ወደ ፍሬወይኒ አሻግራ ተጫዋቿ መረጋጋት ባለመቻሏ ኳሷ ወጥታባታለች፡፡ 13ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት መሰሉ አበራ ከቀኝ የአርባምንጭ የግብ ክልል በቀጥታ ወደ ጎል ስትመታ የአርባምንጯ ግብ ጠባቂ ድንቡሽ አባ ልትቆጣጠር ባለመቻሏ ሣራ ነብሶ ከጎሉ ትይዩ ሆና ብታገኘውም ስታዋለች፡፡

አርባምንጮች የመጀመሪያ ሙከራቸውን 16ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል፡፡ ሰናይት ባሩዳ በቀኝ መስመር በኩል ከመሐል ሜዳ በረጅሙ ያሻማችውን ኳስ መሠረት ወርቅነህ ብቻዋን ሆና ማግኘት ብትችልም አምልጧታል፡፡

17ኛው ደቂቃ ላይ ኤሌክትሪኮች ጎል አስቆጥረዋል፡፡ እፀገነት ብዙነህ በቀጥታ ወደ ጎል የላከችውን ኳስ ሣራ ነብሶ በቀላሉ ከመረብ አሳርፋ ቡድኑን መሪ አድርጋለች፡፡ በድጋሚ መሰሉ አበራ ከቅጣት ምት አክርራ መታ እንደምንም ግብ ጠባቂዋ ያወጣችባት የኤሌክትሪክን የግብ መጠን የምታሳድግ የጠራችዋ ሁለተኛዋ ሙከራ ነበረች፡፡

23ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ባሩዳ አሾልካ በተጫዋቾች መሀል ወደ ቀኝ መስመር ያሳለፈችውን ትዝታ ኃይለማርያም ወደ ጎል ስትመታ የትዕግስት አበራ ስህተት ታክሎ አርባምንጮች ወደ 1ለ1 ተሸጋግረዋል፡፡

አጋማሹ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩ ሁለቱም ቡድኖች የሚያስቆጩ ዕድሎች አምልጧቸዋል፡፡ 40ኛው ደቂቃ ሣራ ነብሶ የአርባምንጭ ተከላካዮችን አምልጣ ወደ ሳጥን ገብታ ወደ ጎል ስትመታ ድንቡሽ አባ ያወጣችባት እንዲሁም በአርባምንጭ በኩል 44ኛው ደቂቃ ሰናይት ባሩዳ በግል ጥረቷ አሾልካ ለመሠረት ወርቅነህ ሰጥታት መሠረት ሁለት የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን አልፋ ከግቡ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝታ ወደ ጎል ለወጠችሁ ተብሎ ቢጠበቅም በቅፅበት አረጋሽ ፀጋ ከኃላ መጥታ አስጥላታለች፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ልቀው የተገኙበት ነበር፡፡ ጎል ለማስቆጠር ከእረፍት መልስ ገና በጊዜ ጥቃት ለመሰንዘር በተደጋጋሚ የአርባምንጭ የግብ ክልል ሲመላለሱ የነበሩት ኤሌክትሪኮች በርከት ያሉ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም በመከላከል ላይ ያመዘኑትን የአርባምንጭ ተጫዋቾች ለማለፍ ግን ተቸግረው ተስተውሏል፡፡ በዚህም ተደጋጋሚ ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቶ ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ሦስተኛ ሆኖ የመጨረስ ዕድሉ የነበረው ኤሌክትሪክ ነጥብ በመጣሉ ደረጃውን ለሀዋሳ ከተማ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ