“ዕድላችን በራሳችን ነው የሚወሰነው” – ጌታነህ ከበደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማዳጋስካርን አራት ለምንም ሲረታ ግሩም የቅጣት ምት ጎል ካስቆጠረው ጌታነህ ከበደ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ኢትዮጵያ ዳግም ከሰባት ዓመታት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ያላትን ተስፋ ያለመለመችበትን ድል በዛሬ ዕለት ማዳጋስካርን አራት ለምንም በመርታት አስመዝግባለች። ቡድኑን በአንበልነት ከመምራቱ በተጨማሪ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የረጅም ዓመታት ልምድ ያለው እንዲሁም የቡድኑን ሁለተኛ ጎል በግሩም ሁኔታ ከቅጣት ምት ያስቆጠረው ጌታነህ ከበደ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ስለዛሬው ጨዋታ እና በቀጣይ ስለሚጠብቃቸው የኮትዲቯር ጨዋታን በተመለከተ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ስለ ጨዋታው ?

“ጨዋታው አሪፍ ነበር ፤ በጥሩ ውጤት በማጠናቀቃችንም ደስተኛ ነኝ።”

የማላዊው የወዳጅነት ጨዋታ ስለነበረው አስተዋጽኦ?

“ባለፈው አዲስ አበባ ላይ ከዛምቢያ ጋር የነበረን የወዳጅነት ጨዋታን ለማሸነፍ በጣም ተቸግረን ነበር፤ ጭራሽ ከሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፈን አንዱን ብቻ ነበር አቻ መውጣት የቻልነው። በአሁኑ የማላዊ ጨዋታ ግን ግቦች አስቆጥረን በማሸነፋችን በዛሬው ጨዋታ በብዙ ተጠቅመናል።”

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ስላስቆጠረው የመጀመሪያው የቅጣት ምት ጎል?

“በጣም ነው ደስ ያለኝ። ምክንያቱም እኛ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከሜዳችን ውጭ ሁለት እድል ይዘን ለመሄድ በዛሬው ጨዋታ ከአንድ በላይ ጎል ያስፈልገን ነበር፤ እኔ ያስቆጠርኩት ሁለተኛ ግብ ቡድኑን ያረጋጋች ግብ በመሆኗ በጣም ደስ ብሎኛል።”

የአፍሪካ ዋንጫውን ለመቀላቀል ስላለን ዕድል?

“በሚገባ ፤ ዕድላችን በራሳችን ነው የሚወሰነው። ምክንያቱም ወደ አይቮሪኮስት ሄደን አቻ ከወጣን በቀጥታ ነው የምናልፈው።”

ስለቡድኑ መንፈስ

“የቡድኑ መንፈስ በጣም አሪፍ ነው ፤ ሁሉም አባል ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ይፈልጋል። በስብስባችን ያሉ ተጫዋቾች በጣም አሪፍ ናቸው ፤ እንደውም በዚህ ሰአት ቢሆን ኖሮ ኒጀርን የምናገኘው በጣም ጥሩ ነበር። ለ7 ወር ያክል በኮሮና ምክንያት አርፈን ስንመለስ ሆነ እንጂ ኒጀርን ሄደን ለማሸነፍ አቅሙ ነበረን ፤ አሁን ላይ የትኛውንም ቡድን ብናገኝ የማሸነፍ አቅሙ አለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ