ለረጅም ጊዜ ከሜዳ መራቅ በአዕምሮ ላይ የሚያደርሰው ጫና

እግር ኳስ ተጫዋቾች ከሚያጋጥማቸው እከሎች ዋንኛው በከባድ ጉዳት ምክንያት ከሜዳ ዘለግ ላለ ጊዜ መገለል ነው፡፡ ይህም በአዕምሮ ጤናቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው፡፡ ከሜዳ በራቁ ቁጥር ብቸኝነት እና ድባቴ ሊሰማቸው ይችላል፡፡ በዛሬው የሶከር ሜዲካል አምዳችን የምንመለከተው ይህንን ጉዳይ ነው፡፡

ከበድ ያሉ ጉዳቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት ወደ ሜዳ ለመመለስ የሚደረጉት ስራዎች ጊዜን የሚወስዱ እና ትዕግስትን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የህክምና ዕርዳታ አልያም ቀዶ ጥገና ከተደረገ በኋላ የሚኖረው የማገገሚያ ጊዜ የስነ ልቦና ጥንካሬን እና ተስፋ አለመቁረጥን ይጠይቃል፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾች ምንም እንኳን ዘለግ ላሉ ጊዜያት ከጨዋታ ቢርቁም በርትተው በመስራት አቋማቸው ሳይወርድ ሲመለሱ እንመለከታለን፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው የባለሙያ እና የቤተሰብ ዕርዳታ ከግል ጥንካሬ ጋር ሲዳመሩ በሚያመጡት ለውጥ ነው፡፡

ሳላዲን ባርጌቾ ከጉዳት አገግሞ መመለስ ከባድ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ “ወደ ራስ ለመመለስ ጊዜ ይወስዳል” በማለት አስቸጋሪዎቹን የጉዳት ጊዜያት ያስታውሳቸዋል፡፡ ልምምድ በመስራት የማገገሚያ ጊዜውን ያሳለፈው ሳላዲን ፊዝዮቴራፒ ከጉዳት ለማገገም እጅጉን ወሳኝ እንደሆነም አክሎ ይናገራል፡፡ ቀዶ ህክምና ከተሰራበት ወቅት ጀምሮ ፊዝዮቴራፒ እየሰራ የነበር መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከዛም በመቀጠል ስነ ልቦና ላይ ሊደርስ ለሚችል ማንኛውም ዕከል የቤተሰብ እና ጓደኛ አብሮነት በጣም አስፈላጊ እንደነበር ይናገራል፡፡

ከሜዳ ለረጅም ጊዜ የራቀው ወንድሜነህ ዓይናለም በበኩሉ የደረሰበትን የጅማት ጉዳት በሚያስታምምበት ወቅት ልምምድ መስራት እና መጽሀፍ ማንበብ ጊዜ ማሳለፊያዎቹ እንደነበሩ ይናገራል፡፡ እርሱም እንደ ሳላዲን ሁሉ የፊዝዮቴራፒ እርዳታ ማግኘቱ እንደጠቀመው ይናገራል፡፡ ከሜዳ ለረጅም ጊዜ መገለል ስነ ልቦና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን አክሎ ይገልጻል፡፡

ተጫዋቾች የቀድሞ ብቃታቸው እንዳለ እና ምንም አይነት የስነ ልቦና ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ሜዳ እንዲመለሱ ከተፈለገ ዘመናዊ የሆነ የማገገሚያ መርሃ ግብር እንደዚሁም አስፈላጊ መሳሪያዎች እና ባለሙያዎች ግዴታ መሟላት አለባቸው፡፡ ክለቦች በበኩላቸው የተጎዱ ተጫዋቾቻቸውን የመንከባከብ ግዴታ አለባቸው፡፡ አንድ ተጫዋች ጉዳት ካጋጠመው በኃላ ሙሉ በሙሉ የሚረሳበት እና በቂውን ትኩረት የማያገኝበት አሰራር ሊቀረፍ ይገባል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ