“እኔ እና ተጫዋቾቼ ኢትዮጵያ ላይ ጨዋታን ማሸነፍ ቀላል እንዳልሆነ እናውቃለን” ኒኮላ ዱፑይ

ከነገው ጨዋታ በፊት የማዳጋስካር ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ እና አምበል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ዋልያዎቹ በነገው ዕለት የማዳጋስካር አቻቸውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይገጥማሉ። ከጨዋታው በፊትም የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች እና አምበሎች የቅድመ ጨዋታ አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል። ማዳጋስካሮችም በዋና አሠልጣኛቸው ኒኮላስ ዱፑይ እና አምበላቸው ማልቪን አድሪያን አማካኝነት ሀሳባቸውን አጋርተዋል። በቅድሚያም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ኒኮላስ ዱፑይ ተከታዩን ብለዋል።

“በተጫዋቾቼ በጣም ደስተኛ ነኝ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስቡ ሙሉ ነው። በጣም አሪፍ ቡድንም ነው። ኮትዲቯርንም 2-1 አሸንፏል። ይህ ደግሞ ለእኛ ከባድ ነገር ይነግረናል። እኔ እና ተጫዋቾቼ ኢትዮጵያ ላይ ጨዋታን ማሸነፍ ቀላል እንዳልሆነም እናውቃለን። ግን ምንም ቢሆን ምንም ተጫዋቾቼ ለመፋለም ባላቸው ዝግጁነት ደስተኛ ነኝ። ሁሉም ተጫዋቾቼ ደግሞ ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ፍላጎት አላቸው። በአጠቃላይ ለነገው ፍልሚያ ዝግጁ ነን። የማዳጋስካርንም ህዝብ ለማስደሰት ተዘጋጅተናል።

“ከኮቪድ-19 እና ከፊፋ ክልከላ መነሻነት ሁሉንም የብሔራዊ ቡድን ስብስብ ማግኘት አልተቻለም። ግን ከፈረንሳይ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና አስተዳደር ጋር ተነጋግረን የተወሰኑ ተጫዋቾችን ባለቀ ሰዓት አግኝተናል። ግን የቡድናችንን አምበል በቡልጋሪያ ባለው ክልከላ ምክንያት ማግኘት አልቻልንም። እንዳልኩት አራት እና አምስት ቋሚ ተጫዋቾችን ባናገኝም ስብስቡ ተፎካካሪ ስለሆነ ችግር አይገጥመንም። ምንም እንኳን የነበረን ጊዜ ያነሰ ቢሆንም ባለን ጊዜ ጥሩ ሥራ ሰርተናል።”

ከ53 ዓመቱ ዋና አሠልጣኝ እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ የተቀላቀለበትን ንግግር በኋላ የቡድኑ አምበል እና የግብ ዘብ ማልቪን አድሪያን አጭሩን ሃሳቡን በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች አጋርቷል።

“የቡድኑ ስሜት አንድ ነው። ለነገውም ጨዋታ ዝግጁ ነን። በጨዋታውም ጥሩ ነገር ይዘን ለመውጣት እንሞንራለን። ለአፍሪካ ዋንጫውም ለማለፍ ጠንካራ ልምምዶችን እና ዝግጅቶችን አድርገናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ