ዋልያዎቹ ማዳጋስካርን አራት ለምንም ሲረቱ የማሳረጊያውን ጎል ከመረብ ያገናኘው ሽመልስ በቀለ ስለወቅታዊ ብቃቱ፣ ስለ ብሔራዊ ቡድኑ እንቅስቃሴ እና ስለ ቀጣይ የእግርኳስ ህይወቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ ይገኛል። በትናንትናው ዕለትም የምድቡ አምስተኛ ጨዋታውን ከማዳጋስካር ጋር ያከናወነው ቡድኑ አራት ግቦችን ተጋጣሚው ላይ አስቆጥሮ በጊዜያዊነት (ኮትዲቯር እና ኒጀር እስኪጫወቱ) የምድቡ መሪ ሆኗል። ቡድኑ ፍፁም የጨዋታ ብልጫ ኖሮት ሲያሸንፍ አንድ ግብ ከመረብ ያሳረፈው ሽመልስ በቀለ ስለወቅታዊ ብቃቱ፣ ስለ ብሔራዊ ቡድኑ አሁናዊ እንቅስቃሴ እና ስለ ቀጣይ የእግርኳስ ህይወቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ የነበረው ትዝታ እና የአሁን ስሜትን እንዴት ታየዋለህ?
“የዛሬ ስምንት ዓመት ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ የተሰማን ስሜት ከባድ ነበር። ለእኔም በእግር ኳስ ዘመኔ የመጀመሪያው ስለነበር በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ለእኔ ብቻም ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝብም ትልቅ ድል ነበር። ያንን ጊዜ ፈፅሞ ልረሳው አልችልም። በጣም ብዙ ነገሮችን የሸፈነ ጊዜ ነበር። ጊዜውን ሳስብ ቀድሞ የሚመጣብኝ ህዝቡ ላይ የተፈጠረው ስሜት ነበር። ኳስ ወዳድነቱ ምን ያህል እንደነበር ደስታውን ከገለፀበት መንገድ መረዳት ትችላለህ። ካሁኑ ወቅት ጋር እያወዳደርኩት ባይሆንም የያኔው እጅግ የተለየ ነበር። አሁን ላይ በኮሮና ምክንያት ደጋፊ ወደ ሜዳ ስለማይገባም ያን ስሜት አጥፍቶት ይሆናል። እውነቱን ለመናገር ያኔ እንደተሰማኝ ያህል አሁን እየተሰማኝ አይደለም። ነገር ግን ባገኘነው ድል በጣም ደስ ብሎኛል። ግን ደግሞ ከመጀመሪያውም በበለጠ እንዲሰማኝ እፈልጋለሁ። ከአምላክ ጋር አሁንም እንደምናልፍ እና ያንን ስሜት መልሼ እንደማገኘው ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህ አጋጣሚ የቡድን ጓደኞቼን ፣ አሰልጣኞቻችንን እና መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ማመስገን እፈልጋለሁ። አሁን ላይ ካለው ነገር አንፃርም መደሰት የሚገባው ህዝብ ነው። ይህ ህዝብ መደሰት ያንሰዋል ብዬ ነው የማስበው። የአምላክ ዕርዳታ ተጨምሮበት እኛ ያለን የእግር ኳስ ክህሎት በሚፈቅደው ሁሉ ኢትዮጵያን ወደ አንድነት ለማምጣት የመጨረሻዋን 90 ደቂቃ እየጠበቅን ነው።”
በሁለቱም ትውልዶች ውስጥ እንደመኖርህ ያሁኑ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍን ያሳካዋል ብለህ ታስባለህ ?
“ያሳካዋል ብዬ አምናለሁ፤ ምክንያቱም ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አሉ። በጣም ወጣት ተጫዋቾችም አሉ። ደግሞም ፕሪምየር ሊጉ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ማግኘቱ የተጫዋቾችን ችሎታ እያወጣ ይመስለኛል። ይህ ነገር በፊት ኖሮ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ነገር መሥራት ይቻል ነበር ብዬ አምናለሁ። እኔ በሁለቱም ትውልዶች ውስጥ አለሁ። አሁን ካሉት ወጣት ልጆች ጋር አብረን በመሥራትም ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ጥሩ ነገር እንሠራለን ብዬ አስባለሁ። በእርግጠኝነት ያሳኩታል ብዬም አምናለሁ።”
በቅርብ የክለብ እና የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ወደ ጎል አስቆጣሪነት የመጣህበት የተለየ ምክንያት ይኖራል ?
“ምንም የተለየ ነገር ኖሮ አይደለም። ፈጣሪ የሰጠኝ ክህሎት አለ። ያንን ለማንም አሳልፌ አልሰጥም፤ የተሰጠኝን ይህን ዕድል በአግባቡ እጠቀማለሁ። የተሰጠኝን ልምምድ በአግባቡ እሰራለሁ። ያንን ካደረክ ደግሞ ጨዋታ ላይ ነገሮች ቀላል ይሆንሉሀል። ለእያንዳንዱ ልምምድ እና ጨዋታ ትኩረት ከሰጠህ እንዲሁም በራስህ ላይ ዕምነት ካሳደርክ ምንም ነገር ማድረግ ትችላለህ። ሁሌም ወደ አዕምሮዬ ማስገባው ይህንን ነው። አሁን ባለሁበት ክለብ ምስር አል ማቃሳ ውስጥም ጎል እያገባው ነው። ቡድኑም ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ፤ ጥሩ አሰልጣኝም አለው። ይህ የሆነው አንድም ቡድኑ ኳስ ይዞ የሚጫወት በመሆኑ እና የምፈልገው ቦታ ላይ በነፃነት እንድጫወት ዕድሉ ስለተሰጠኝም ነው። አሁንም ራሴን ትልቅ ደረጃ ማድረስ ፈልጋለሁ። ሰዎች ብዙ ጊዜ ዕድሜያቸው በሄደ ቁጥር ዝቅ የሚሉበት ነገር አለ። እኔ ራሴን ወደዛ ውስጥ መክተት አልፈልግም። ሁሉም ሰው ስራዬን አይቶ እንዲመሰክር ነው የምፈልገው። ያንን ለማድረግ ጠንክሬ እሰራለሁ ፤ ራሴን ጠብቃለሁ። የዛን ያህል ሁሉንም ሰውም አከብራለው ፤ ለትንሹም ለትልቁም አክብሮት አለኝ። እና ለእያንዳንዱ ነገር ትኩረት እሰጣለሁ። ዋናው ነገር ግን ሁሉም ነገር ያስደስተኛል ፤ ኳስ በጣም ነው የሚያስደስተኝ። ብሔራዊ ቡድን ስጠራ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠራሁ ያህል ነው የሚሰማኝ። ይሄ ሁሉ ነገር ከአዕምሮዬ እንዲጠፋ አልፈልግም። በቃ ጫማዬን ስሰቅል ስለሌላው ማስብበት ጊዜ ይኖራል ። አሁን ላይ ግን የማስበው ኳስን እና ኳስን ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ የተለየ ነገር የለውም። ወደ ጎል ስሄድ ራሴን አዘጋጅቼ ነው የምሄደው። እንደማስቆጥር ለራሴ አምኜ ነው የምሄደው። ልምምድ ላይም እዚህ ላይ እሰራለሁ። ከዛም መነሻ ክለቤ ላይ ባለፉት 14 ጨዋታዎች ስድስት ጎሎችን አስቆጥሬያለሁ ፤ ብዙ ግብ የሆኑ ኳሶችም አመቻችቻለሁ። ነገር ግን ከእነዚህ ሁሉ ማዳጋስካር ላይ ማግባቴ ለእኔ የተሻለ ነው። ሀገር ነውና የሚቀድመው ይህንን ግብ ማስቆጠሬ አስደስቶኛል። በአራታችንም ጎል ቡድኑ አንድ ሆኖ ይህንን ውጤት አምጥቷል። በተቻለ መጠንም በቀጣዩ ጨዋታ ጥሩ ነገር ሰርተን ሀገራችን ኢትዮጵያን ደስ እናሰኛለን ብዬ አስባለሁ።”
ምስር አል ማቃሳን በአምበልነት እያገለገልክ ትገኛለህ …
“አምበል መሆን ለእኔ ትልቅ ክብር ነው። ሀገር ውስጥ ያላገኘሁትን ክብር ከሀገር ወጥቼ ባሳየሁት ብቃት አግኝቻለሁ። ይሄ ለእኔ በጣም ትልቅ ነገር ነው። በእግር ኳስ ህይወትህ የምታስቀምጣቸው ስኬቶች አሉ። በእነዚህ ስኬቶች ደግሞ ይሄኛው ነገር ለእኔ ትልቅ የራስ መተማመን የሚሰጠኝ ነው። በፔትሮጀት ክለብ ሁለት ዓመታትን በአንበልነት ጨርሼ አሁን ላለሁበት ክለብ እንድገባ የሆነው በፀባዬ እና በአምበልነት አቅሜ ነው። አምበል መሆን ከባድ ኃላፊነቶች አሉት። እኔ ግን ከሀገሬ ወጥቼ የሚገጥሙኝን ፈተናዎች አልፌ አምበል በመሆኔ በጣም እኮራለሁ። በአጠቃላይ ስኬት ሲመጣ በጣም ደስ ይላል። ግን ስኬት ሲመጣ ራስን ከፍ ማድረግ አያስፈልግም። ገና እንደምትሰራ ማሰብ አለብህ።”
በግብፅ ሊግ ከሀምሳ በላይ ግቦችን በማስቆጠር ብቸኛው ኢትዮጵያዊም ሆነሀል…
“በግብፅ ሊግ እኔ ብቻ አልነበረም ስጫወት የነበረው። እነ ጋቶች፣ ዑመድ እና ሳልዓዲንም ነበሩ። አሁን ግን እኔ ብቻ ነኝ። በዚህም በጣም አዝናለሁ። እንደምታቀው ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ኳስ የሚችሉ እና ከእኔ በልጠው የተሻለ ደረጃ መቀመጥ የሚችሉ ተጫዋቾች አሉ። አሁንም ግን የእኔን ነገር አይተው የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ እፈልጋለሁ። እንዳልኩት ግብፅ ብቸኛ መሆኔ ቢሰማኝም እራሴን ደስተኛ እያደረኩ ነው እያሳለፍኩ ያለሁት። እንዳልከውም በግብፅ ባለኝ የ7 ዓመት ቆይታ ወደ 57 ጎሎችን አስቆጥሬያለሁ። ይህ ደግሞ የመጣው በምሰራው ሥራ ነው። እኔ አጥቂ አደለሁም። አማካይ ነኝ። ግን በማገኘው እድል ይሄንን ያህል ጎሎችን ማስቆጠሬ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው። ቢሆን እና ቢሳካልኝ አውሮፓ ወጥቼ መጫወት ብችል ደስ ይለኛል። ምንም ቢሆን ግን ፈጣሪ እኛ እንድንደርስ የሚፈቅድልን ቦታ አለ። አሁን የፈቀደልኝ ቦታ ላይ በመገኘቴ ደግሞ እርሱን አመሠግናለሁ።”
በግብፅ የሚኖርህ ቀጣይ ቆይታ?
“ግብፅ ሰባት ዓመት ቆይቻለሁ። አሁን ያለኝ ኮንትራት የሚጠናቀቀው ክረምት መውጫ ላይ ነው። ክለቤም ኮንትራቴን ለአንድ ዓመት እንዳድስ እየጠየቀኝ ነው። ሌሎች ክለቦችም እየፈለጉኝ ነው። ግን ሀገሬ መጥቼ ብጫወት ደስተኛ የምሆንባቸው ነገሮች አሉ። ምክንያቱም ቤተሰብ፣ ጓደኛ እንዲሁም ሌሎች የምትፈልጋቸው ነገሮች እዚህ አሉ። ብዙ ጊዜ እግር ኳስ ተጫዋች ስኬትን ብቻ እየፈለገ ሲሄድ የራሱ ህይወት ይጠፋዋል። እርግጥ ሥራን ማክበር ጥሩ ነው። ግን ደግሞ በሁሉም ነገር ደስተኛ ሆኖ መስራት የተለየ ስሜት አለው። እኔ የተሻለ ደረጃ ደርሻለሁ። የተሻለ ገቢም አግኝቻለሁ። ይህንን ደግሞ አሁን ላይ ሀገር ውስጥም እንደማገኝ እርግጠኛ ነኝ። ግን በዋናነት አሁን ላይ ደስተኛ የሚያደርገኝ ሀገር ውስጥ መጥቼ ብቻወት ነው። ይህንን ስሜቴን ደግሞ ራሴን ካልሆነ ማንም ሊያውቀው አይችልም። የሚፈጠረውን ነገር አላቅም። ወደ ሀገሬ ተመልሼ መጫወት የምችልበት ዕድሎች ይፈጠራሉ። ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ፈጣሪ ጤና ከሰጠኝ አንድ ዓመት በግብፅ የምቀጥል ይመስለኛል። ግን ግብፅ ላይ አሁን ያለው ፖለቲካም ጥሩ ስላልሆነ ወደ ሀገሬ የምመለስበት ዕድል ይኖራል። ወደ ሀገሬ ስመጣ ግን ብቃቴ ወርዶ አልያም ሌላ ነገር ፈልጌ አደለም። መጫወት በደንብ እቻላለሁ። ከዚህ በኋላ ለአምስት ዓመት በግብፅ መቆየት እችላለሁ። ግን እኔ ይሄን ያህል መቆየት አልፈልግም። ምክንያቱም የራሴ ህይወት አለኝ። የሚናፍቀኝ ብዙ ነገር አለ። ስለዚህ ቢበዛ አንድ ዓመት ነው በግብፅ የምቆየው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ