የድሬዳዋ ዝግጅት ወቅታዊ መረጃዎች

ቀጣዮቹን ሠላሳ የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች የምታስተናግደው ድሬዳዋ እና ስታድየሟን ዛሬ አመሻሽ ላይ ቃኝተን ተከታዮቹን መረጃዎች እንካችሁ ብለናል።

የሀገራችን የመጀመሪያ ደረጃ የሊግ ውድድር ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ ሲካሄድ ቆይቷል። በቤት ኪንግ የተሰየመው ውድድሩ ሦስት ከተሞችን አዳርሶ ከፊቱ የሚገኙትን አምስት የጨዋታ ሳምንታት ለመከወን ድሬዳዋ ደርሷል። በርካታ አዳዲስ ነገሮችን እያስመለከተን በዘልቀው ፉክክርም ከጨዋታ ሰዓት አንፃር ለውጦች የተደረጉበት የምስራቋ ከተማ ቆይታ ምን ይዞ እንደሚመጣ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል። ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች የድሬው ቆዮታ ከመጀመሩ አሰድሞ በዋዜማው ያስተዋልናቸውን የተወሰኑ ነጥቦችም እንዲህ ለማንሳት ወደናል።

* የተለመዶው ሞቃታማ አየሯ ያልተለያት ድሬዳዋ ዛሬም ጋል ብላ በእግር ኳሳዊ መንፈስ ውስጥ አምሽታለች። የተለያየ ክለቦች አርማዎችን የያዙ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ አንዳንድ ክፍሎች መታየታቸው የውድድሩን ጠረን ያላበሳት ሲሆን በመልካም የፀጥታ ሁኔታ ላይ ሆና የነገዎቹን ጨዋታዎች በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።

* በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑት 13 ክለቦች ሙሉ ለሙሉ በድሬዳዋ ከትመዋል። በከተማዋ ዘለግ ላለ ጊዜ በመቆየት ወላይታ ድቻ ቅድሚያውን ሲወስድ ፋሲል ከነማ ደግሞ ዛሬ ማምሻውን ድሬ በመድረስ የመጨረሻው ክለብ ሆኗል።

* በድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር አስተባባሪነት ደጋፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ባነር በመያዝ እንግዶቻቸውን በመቀበል ሽር ጉድ ውስጥ ያሳለፉ ሲሆን የከተማዋን ጥንታዊ የባቡር ትራንስፖርት ከባቢ ሼማንደፍርን በማስጎብኘት መልካም መስተንግዶን አሳይተዋል።

* የሊግ ካምፓኒው ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፉ እና የሊግ ካምፓኒው የውድድር ሰብሳቢ ዶ/ር ተገኔ ዋልተንጉስ የውድድሩ የበላይ መሪ በመሆን ወደ ድሬዳዋ መጥተዋል።

* በአቀባበሉ ሌላ ክፍል የከተማዋ አስተዳደር ማምሻውን ለየክለቦቹ አመራሮች ፣ አሰልጣኞች፣ አምበሎች ፣ የሱፐር ስፖርት ተወካዮች እና ሌሎች የውድድሩ አካላት የራት ግብዣ አድርጓል።

* ከከተማዋ የአየር ፀባይ አንፃር ከወትሮው (ረፋድ አራት ሰዓት እና ከሰዓት ዘጠኝ ሰዓት) በተለየ ለውጦች ተደርገውበት የነበረው የጨዋታ ጊዜ ጉዳይ ወደ ረፋድ አስር ሰዓት እና ምሽት አንድ ሰዓት እንዲመጣ ተደርጓል። ዛሬ በተለይም ምሽት አንድ ሰዓት ላይ የነበረው የአየር ሁኔታ ጨዋታ ለማድረግ መልካም ሆኖ ብናገኘውም የውሳኔው ዘግይቶ መደረግ ከቅድመ ዝግጅት አንፃር ዕክሎች እንዳይፈጠሩ መጠነኛ ስጋት ይጭራል።

* ዛሬ ከሰዓት በድሬዳዋ ስታድየም በተገኘንበት አጋጣሚ የመጨረሻ ዝግጅቶች ሲደረጉ ተመልክተናል። ከእነዚህም ውስጥ የመጫወቻ ሜዳውን መስመሮች ማስመር ፣ የወንበሮች ፅዳት ፣ የመረብ ዝርጋታ እና የምሽቱን ጨዋታ በተገቢው ሁኔታ ለመቅረፅ ይቻል ዘንድ የሚረዱ የፓውዛ መብራቶች ገጠማ ይገኙበታል።

* ከባህር ዳሩ ውድድር በቀር በመጫወቻ ሜዳ ዝግጅት ረገድ እንከን ያላጣው ሊጉ ድሬዳዋ ላይም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይገጥመው ያሰጋል። የስታድየሙ መጫወቻ ሜዳ በአመዛኙ አረንጓዴ ገፅታ ቢኖረውም ወጣ ገባነት የሚታይበት እና አልፎ አልፎም ሳር አልባ ቦታዎች ያሉት መሆኑ ከጨዋታ ፍሰት እንዲሁም መስመሮችን በቀጥታ ከመመልከት አንፃር በዳኝነት ላይ ተፅዕኖ እንዳይኖረው ያሰጋል።

* በኢትዮጵያ ዳኞች ኮሚቴ በኩል 13 ዋና እና 13 ረዳት ዳኞች ለውድድሩ ዝግጁ ሆነው ድሬ ገብተዋል። ከዋና ዳኞች መካከል ዛሬ ማምሻውን በስታድየሙ ሜዳ ላይ በግሉ ልምምድ ሲያከናውን የተመለከትነው በአምላክ ተሰማ ፣ ሊዲያ ታፈሰ ፣ ለሚ ንጉሴ እና ኃይለየሱስ ባዘዘው ከረዳቶች ደግሞ ሸዋንግዛው ተባበል ፣ ክንዴ ሙሴ እና ተመስገን ሳሙኤል ኢንተርናሽናል ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ፌደራል ዳኞች ናቸው።

* ውድድሩን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የሚያስተላልፈው ሱፐር ስፖርት አባላት ማሰራጫ ጣቢያዎችን ከያዙት ተሽከርካሪዎች ጋር በድሬዳዋ ስታድየም በመገኘት አመሻሽ ላይ የገመድ ዝርጋታ እና ሌሎች የቴክኒክ ቅድመ ዝግጅታቸውን አድርገዋል።


* የምሽቱን ጨዋታ በጥራት ለመቅረፅ በቂ ብርሀን መኖሩን ለማረጋገጥ ማምሻውን ሙከራዎች ተደርገዋል። ነገር ግን ሙከራው አሁንም አጥጋቢ ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም። የፓውዛው ጉልበት እና አቅጣጫ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ ተመጣጣኝ ብርሀን የማድረስ ችግር የተስተዋለበት ሲሆን የማስተካከል ሙከራውም እስካሁን እንደቀጠለ ነው። ነገር ግን ብቸኛው የማስተካከያ አጋጣሚ ያለው ዛሬ ላይ ብቻ በመሆኑ ነገ ምሽት ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማን የሚያገናኘው ጨዋታ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን የማግኘቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ