ሪፖርት | ዋልያዎቹ ማዳጋስካርን በመረምረም ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋቸውን አለምልመዋል

ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኙት ዋልያዎቹ ማዳጋስካርን ባህር ዳር ላይ አስተናግደው በፍፁም የጨዋታ ብልጫ አራት ለምንም አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለወሳኙ ጨዋታ ተክለ ማሪያም ሻንቆ፣ አስራት ቱንጆ፣ ያሬድ ባየህ፣ አስቻለው ታመነ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ሽመልስ በቀለ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ጌታነህ ከበደ እና አቡበከር ናስርን በማሰለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ከረጃጅም እና ከቆሙ ኳሶች አስደንጋጭ ሙከራዎችን በማድረግ ጨዋታውን የጀመሩት ማዳጋስካሮች በ12ኛው ደቂቃ ካሩለስ አንድሪያማሂቲኖሮ ከቅጣት ምት በመታው ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተቃራኒው ኳስን በተሻለ ተቆጣጥረው ሲጫወቱ የነበሩት ዋልያዎቹ በበኩላቸው በ17ኛው ደቂቃ ለግብነት የቀረበ ሙከራ ሰንዝረው ነበር። በዚህ ደቂቃም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ረመዳ የሱፍ ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ተከላካዮች አምክነውበታል።

ጨዋታው ቀጥሎም በ19ኛው ደቂቃ ወደ ማዳጋስካሮች የግብ ክልል የደረሱት ዋልያዎቹ መሪ የሆኑበትን ኳስ አስቆጥረዋል። በዚህም ጌታነህ ከበደ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ለአማኑኤል ያቀበለውን ኳስ የመስመር አጥቂው በጥሩ እርጋታ ኳሱን ከመረብ አዋህዶታል። ለተቆጠረባቸው ጎል ወዲያው ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ማዳጋስካሮች ፈጣን ሽግግር በማድረግ የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ጥረው መክኖባቸዋል።

ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ የቀጠለላቸው የአሠልጣኝ ውበቱ ተጫዋቾች በ34ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድገዋል። በዚህ ደቂቃም ላላይና አቡበከር ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፎታል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት የቀጠሉት ማዳጋስካሮች 39ኛው ደቂቃ ላላይና በመታው የቅጣት ምት ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል።

ፍፁም የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው ባለሜዳዎቹ አጋማሹ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም አቡበከር ከሱራፌል ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ራሱን ነፃ በማድረግ ያገኘውን የመጨረሻ ኳስ በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ግብነት ቀይሮታል። አጋማሹም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሦስት ለምንም መሪነት ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ለማስቆጠር ከራሳቸው ሜዳ ወጣ ብለው መጫወት የጀመሩት ማዳጋስካሮች በ60ኛው ደቂቃ የሚመሩበትን የጎል ውጤት ለማጥበብ የሚያስችላቸውን ዕድል አግኝተው ነበር። በዚህ ደቂቃም ካሩለስ አንድሪያማሂቲኖሮ በኢትዮጵያ ተከላካዮች የተፈጠረን ስህተትን በመጠቀም ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ መትቶት ተክለማርያም አድኖበታል።

ቀዝቀዝ ብለው ይህኛውን አጋማሽ የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በመጀመሪያው አጋማሽ ሲያደርጉት የነበረውን ጥቃት ጋብ አድርገው ታይተዋል። በተቃራኒው የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ የማጥቃት ሃይላቸውን ለማጠናከር የሞከሩት ኒኮላ ዱፑይ በ72ኛው ደቂቃ ቡድናቸው ሌላ ግብ የማስቆጠሪያ ዕድል አግኝቶ ነበር። በዚህም በጨዋታው ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ሲያገኝ የነበረው ካሩለስ አንድሪያማሂቲኖሮ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም አጋጣሚውን ተክለማርያም አምክኖታል።

ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረው የቀጠሉት ባለሜዳዎቹ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት አራተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በ86ኛው ደቂቃም የቡድኑን ሁለተኛ ጎል በግሩም ሁኔታ ያስቆጠረው ጌታነህ ከሌላኛው ግን አስቆጣሪ አቡበከር የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታው ማልቪን ሲተፋው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሽመልስ በቀለ ኳሱን መረብ ላይ አዋህዶታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በዋልያዎቹ ፍፁም የጨዋታ ብልጫ ታጅቦ አራት ለምንም ተገባዷል።

ውጤቱን ተከትሎ ጣፋጭ ድል የተቀዳጁት ዋልያዎቹ የሰበሰቡትን ነጥብ ዘጠኝ በማድረስ የምድቡ መሪ ሆነዋል(ኮትዲቯር እና ኒጀር ቀሪ ጨዋታ አላቸው)። በዛሬው ጨዋታ ሦስት ነጥብ እና አራት የግብ ክፍያ ያስረከቡት ማዳጋስካሮች ደግሞ ከሁለተኛ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ