“ከጎሎቹ በላይ የተቆጠሩበት መንገድ አስደስቶናል” – ውበቱ አባተ

የዋልያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከጣፋጩ ድል በኋላ ለጋዜጠኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት የምድቡ አምስተኛ ጨዋታውን ከማዳጋስካር አቻው ጋር አከናውኗል። ቡድኑም ወሳኙን ጨዋታ በፍፁም የጨዋታ ብልጫ አራት ለምንም ረቷል። ከጨዋታው በኋላም የዋልያዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው…?

“ተጋጣሚያችን ማዳጋስካር የምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ነው የገጠመን። በመጀመሪያ ግንኙነታችንም አንድ ለምንም አሸንፎን ነበር። ስለዚህ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የግዴታ እነሱ ካሸነፉን ጎል በላይ አግብተን የእርስ በእርስ ግንኙነትታችንን በበላይነት ማጠናቀቅ ነበረብን። በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ አጥቅተን ለመጫወት ጥረናል። ይህም ደግሞ ተሳክቶልን ሦስት ጎሎችን ማስቆጠር ችለናል። በእርግጥ ከባድ ፈተና ነበር። ቢሆንም ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ሦስት ጎሎችን ማስቆጠራችን ነገሮችን አቅሎልናል። ከእረፍት በኋላ ደግሞ ጨዋታውን ተቆጣጥረን አንድ ጎል አክለን ውጤቱን አስፍተናል። ይሄ ደግሞ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ብሔራዊ ቡድን የተሻለ የራስ መተማመን የሚፈጥር ነው። በአጠቃላይ በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

ስለ ተጋጣሚ ቡድን እንቅስቃሴ…?

“ተጋጣሚያችን ውጤቱን በጣም ይፈልጉት ነበር። አቻም መውጣት ለእነሱ የተሻለ ነገር እንደሆነ ይገባናል። በዚህም ተከላክሎ ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት ይዘው እንደሚመጡ አስበናል። በጨዋታውም ያየነው ይህንኑ ነው። በአካላዊ ብቃት እና በአየር ላይ ኳስ ነበር ስንቸገር የነበረው። ከዚህ ውጪ ግን እኛ ሙሉ ለሙሉ የተሻለ ነገር ነበረን። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጠንካራ ፍልሚያ ነበር። ነገርግን ጎሎችን ካስቆጠርን በኋላ ነገሮች ቀለውልን ተጫውተናል።

ስለ ግብ ጠባቂው ተክለማርያም…?

“ግብ ጠባቂ እንደ ሌሎቹ የሜዳ ላይ ተጫዋች አይደለም። የራስ መተማመኑን ለማምጣት ደግሞ ጨዋታዎች ያስፈልጉታል። ተክለማርያም በክለቡ ከጨዋታ የራቀ ተጫዋች ነው። ዛሬም የነበረው ነገር ከዚህ ጋር የሚገናኝ ነው እንጂ የብቃት ጉዳይ አይደለም። በሂደትም ወደ ብቃቱ እንደሚመለስ እርግጠኛ ነኝ። ዛሬ ግን ያሳየው ነገር ከበቂ በላይ ነው።

ግቦቹን የተለያዩ ተጫዋቾች ስለማስቆጠራቸው…?

“በመጀመሪያ የተለያዩ ተጫዋቾች ግቦችን ማስቆጠራቸው የቡድኑን የጎል ማግባት አማራጭ ያሰፋልናል። ተጫዋቾቹም የራስ መተማመናቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። ጎሎቹ ከመግባታቸው በላይ ግን የተቆጠሩበት መንገድ ለእኛ ትልቁ ነገር ነው። ይህንንም መሠረት አድርገን ስንሰራ ስለነበረ ጎሎቹ የተቆጠሩበት መንገድ ነው ሲያስደስተን የነበረው። ይህንኑ አጨዋወት የምንከተል ከሆነም ሌሎቹም ተጫዋቾች ግብ ማግባት እንደሚችሉ እርግጠኞች ነን። ከምንም በላይ ግን ይህ ጉዳይ ለተጫዋቾቹ የራስ መተማመን ጥሩ ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ