“ከኮትዲቯሩ ጨዋታ የሚያስፈልገውን ነጥብ አግኝተን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ እንጥራለን” – ውበቱ አባተ

የዋልያዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ ወደ ካሜሩን ለማምራት አንድ ነጥብ የቀረው ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫው የሚያሳልፈው አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች አልፎ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ እየተንደረደረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት የማዳጋስካር አቻውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አስተናግዶ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር አራት ለምንም አሸንፏል። ከጨዋታው መገባደድ በኋም ከጋዜጠኞች ጋር የድህረ-ጨዋታ ቆይታ የነበራቸው የዋልያዎቹ ዋና አሠልጣኝ ስለ ቀጣዩ የኮትዲቯር ጨዋታ ተከታዩን ብለዋል።

“ይህ ቡድን ከዛምቢያው የወዳጅነት ጨዋታ ጀምሮ እየተገነባ የመጣ ቡድን ነው። ካለፈው የማዳጋስካር እና ኮትዲቯር ጨዋታ ጀምሮም የተሰራ ነገር አለ። እኛም ይህንን ነው እያስቀጠልን ያለነው። ለኮትዲቯሩም ጨዋታ ጥሩ ዝግጅት አድርገን የሚያስፈልገውን ነጥብ አግኝተን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ እንጥራለን። ይህንንም ለማሳካት የሚያስችል አቅም አለን ብዬ አስባለሁ።

“በእርግጠኝነት አቢጃን የምንሄደው ለኳስ ጨዋታ ነው። ለኳስ ጨዋታ ደግሞ ተጋጣሚን አግዝፎ ማየት አያስፈልግም። ሁሉንም ቡድን የሚገዛው ኳስ ነው። ስለዚህ ምንም የሚያስፈራ ነገር የለውም። ማሳደግ የምፈልገውን ነገር በጨዋታው እጠብቃለሁ። ውጤቱን ደግሞ አብረን እናያለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ