ከወሳኙ ድል በኋላ ዋልያዎቹ ወደ ሥራ ተመልሰዋል

በዛሬው ዕለት ጣፋጭ ድል ማዳጋስካር ላይ የተቀዳጁት ዋልያዎቹ በደቂቃዎች ውስጥ ለቀጣዩ ጨዋታ መዘጋጀታቸውን ጀምረዋል።

በ2021 ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከኒጀር፣ ኮትዲቯር እና ማዳጋስካር ጋር ተደልድለው የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እየከወኑ የሚገኙት ዋልያዎቹ በዛሬው ዕለት የማዳጋስካር አቻቸውን ባህር ዳር ላይ ጋብዘው አራት ለምንም ረተዋል። እጅግ ወሳኝ ከነበረው ጨዋታ በኋላም የቡድኑ ስብስብ ለቀጣዩ የኮትዲቯር ጨዋታ ዝግጅት ማድረግ መጀመሩን ተመልክተናል።

ጨዋታው 12 ሰዓት ከተጠናቀቀ በኋላም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከረዳቶቻቸው ጋር በመሆን በጨዋታው በመጀመሪያ ተሰላፊነት ያልነበሩ ተጠባባቂ ተጫዋቾችን (ተቀይረው የገቡትንም ያካትታል) እና ከጨዋታው ውጪ የነበሩ ሁለት ተጫዋቾችን (ፍሬው ጌታሁን እና ወንድሜነህ ደረጄን) በማካተት ለ40 ደቂቃዎች የዘለቀ የልምምድ መርሐ-ግብር አከናውኗል። ከኳስ ጋር የተገናኘ ቀለል ካለው አጠቃላይ የቡድኑ ልምምድ በኋም ሀይደር ሸረፋ፣ ሱሌማን ሀሚድ እና ይሁን እንዳሻው ተጨማሪ ልምምዶችን በተናጥል ሲከውኑ አስተውለናል።

በጊዜያዊነትም ቢሆን የምድቡ መሪ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነገ ዘጠኝ ሰዓት ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዝ ሰምተናል። ስብስቡም አንድ ቀን አዲስ አበባ ካደረ በኋላ ዓርብ 37 ልዑካንን በመያዝ ወደ ኮትዲቯር አቢጃን እንደሚጓዝ አረጋግጠናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ