ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአሠልጣኙ ጋር መለያየቱን ይፋ አድርጓል

ያለፉትን ሦስት ዓመታት ያለ ዋንጫ የዘለቁት ፈረሰኞቹ ከፍተኛ ጫና ውስጥ የቆዩት ማሒር ዴቪድስን መሸኘታቸው በይፋ አስታውቀዋል።

የ27 ጊዜ ኢትዮጵያ ሻምፒዮኑ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ወደ ዋንጫ ለመመለስ ጀርመናዊው ኤርነስት ሚደንድሮፕ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አድርገው ውድድሩን መጀመራቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ አሠልጣኙ በውል ባልታወቀ ምክንያት ከክለቡ ከተለያዩ በኋላ ለምክትል አሠልጣኝነት ኢትዮጵያ የደረሱት ደቡብ አፍሪካዊው ማሒር ዴቪድስ የዋና አሠልጣኝነት መንበሩን ተረክበው ቡድኑን ሲያሰለጥኑ ቆይተዋል።

ቡድኑን ለ15 ጨዋታዎች የመሩት አሠልጣኙ ሰባት ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ማገባደድ ቢችሉም ባስመዘገቡት አምስት የአቻ እና ሦስት የሽንፈት ውጤቶች ጫና ውስጥ ገብተው ነበር። በተለይም ጥሩ የቡድን ስብስብ የነበረው ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር መቸገሩ የቡድኑን ደጋፊዎች ሲያስከፋ ቆይቷል። ይህንን ተከትሎም የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ ከአሠልጣኙ ጋር የጋራ ስምምነት ፈፅሞ አሠልጣኙ ከክለቡ እንዲለያዩ መደረጉን የክለቡ ልሳን የሆነው “ምን ጊዜም ጊዮርጊስ” የሬድዮ ፕሮግራም አስታውቋል። ማሒር ዴቪድስን ተክተውም ከቀናት በፊት ከተስፋ ቡድኑ ወደ ዋናው ቡድን ዳግም የተመለሱት አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድኑን እንደሚያሰለጥኑ ታውቋል።

በተያያዘ ዜና በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ያልነበረው ግብ ጠባቂው ፓትሪክ ማታሲ ይድነቃቸው ተሰማ ልምምዱን እያከናወነ የሚገኘውን ስብስብ መቀላቀሉ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ